ቀጥታ፡

የአፍሪካ ዋንጫን ለበርካታ ጊዜ ያዘጋጁ ሀገራት

የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ 68 ዓመታትን አስቆጥሯል። እ.አ.አ በ1957 የተካሄደውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ ያዘጋጀችው የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሱዳን ናት።

በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ 19 ሀገራት ውድድሩን ለብቻ ወይም በጣምራ አዘጋጅተዋል።

ግብጽ የአፍሪካ ዋንጫን አምስት ጊዜ በማስተናገድ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። ካዘጋጀቻቸው ውድድሮች መካከል ሶስቱን በሀገሯ አስቀርታለች።

የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና አራት ጊዜ ውድድሩን በማዘጋጀት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ከዚህ ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ዋንጫውን አንስታለች።

ኢትዮጵያ እና ቱኒዚያ በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅተዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1962 ባዘጋጀችው ሶስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ግብጽን በፍጻሜው 4 ለ 2 በመርታት ብቸኛ ዋንጫውን አንስታለች።

እ.አ.አ በ1968 ባዘጋጀችው ስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋንጫውን አንስታለች።

ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጀችው እ.አ.አ በ1976 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን በፍጻሜው ሞሮኮ ጊኒን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።

ሞሮኮ፣ ካሜሮን፣ ሱዳን፣  ኮትዲቯር፣ ጋቦን፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅተዋል።

የዘንድሮውን ጨምሮ ከ35ቱ የአፍሪካ ዋንጫዎች መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው በጣምራ የተዘጋጁት።

ሞሮኮ እ.አ.አ 1988 ካዘጋጀችው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ውድድሩን በድጋሚ የማስተናገድ እድል ተሰጥቷታል።

እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን 36ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ታንዛንያ በጣምራ ያዘጋጃሉ።

ይህም ሀገራቱ ውድድሩን ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ የማዘጋጀት እድል ሰጥቷቸዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2029 የሚካሄደውን 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም