ማንችስተር ሲቲ ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ሲቲ ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2018 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ ማንችስተር ሲቲ ከቼልሲ በኢትሃድ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ማንችስተር ሲቲ በ41 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ቼልሲ በ30 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ57ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 56 ጨዋታዎች ቼልሲ 27 ጊዜ ሲያሸንፍ፣ ማንችስተር ሲቲ 20 ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በነበራቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት ማንችስተር ሲቲ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።
ማንችስተር ሲቲ በ19ኛ ሳምንት ከሰንደርላንድ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
ከአሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ጋር የተለያየው ቼልሲ በበኩሉ ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
ማንችስተር ሲቲ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት መልሶ ወደ አራት ዝቅ ያደርጋል።
ቼልሲ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
የ40 ዓመቱ ማይክል ኦሊቨር ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ሊድስ ዩናይትድ ከማንችስተር ዩናይትድ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 እና ፉልሃም ከሊቨርፑል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከሰንደርላንድ፣ ኤቨርተን ከብሬንትፎርድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።