የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ 12 ጨዋታዎችን አከናውኖ አራት ጊዜ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ በ16 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 12 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ሲያሸንፍ ሽንፈት ያስተናገደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አራት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
ሲዳማ ቡና በ25 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ሲዳማ ካሸነፈ መሪነቱን ያጠናክራል።
ሀድያ ሆሳዕና ድል ከቀናው አራተኛ ተከታታይ የሊግ ድሉን ያስመዘግባል።
ነጌሌ አርሲ ከመቻል ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ በውድድር ዓመቱ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ አምስቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል። በአራቱ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 19 ነጥብ በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው መቻል በሊጉ ካከናወናቸው 12 ጨዋታዎች መካከል በአራቱ ድል ሲቀዳጅ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። ቡድኑ በ20 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው ነጌሌ አርሲ በድል ጉዞ ለመቀጠል፣ መቻል ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ሸገር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ12 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ15 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሸገር ከተማ ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከምድረ ገነት ሽሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ ቡና በ15 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።
ምድረ ገነት ሽሬ በ14 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ምድረ ገነት ሽሬ ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።