ቀጥታ፡

በጥሎ ማለፉ አዘጋጇ ሞሮኮ ከታንዛንያ ደቡብ አፍሪካ ከካሜሮን የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። 

አዘጋጇ ሞሮኮ ከታንዛንያ ምሽት አንድ ሰዓት በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


 

ሞሮኮ በምድብ አንድ ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 

የምስራቅ አፍሪካዋ ታንዛንያ በምድብ ሶስት በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ጥሎ ማለፍ ገብታለች።

ሁለቱ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ኮትዲቯር እ.አ.አ በ2023 ባዘጋጀችው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አራት ተገናኝተው ሞሮኮ ታንዛንያን 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ሮማን ሳይስ፣ አዝዲን ኡናሂ እና የሱፍ ኤን-ኔይስሪ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሶስቱም ተጫዎቾች በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የሞሮኮ ስብስብ ውስጥ ይገኛሉ።

ታንዛንያ ወደ ሩብ ለፍጻሜ ለመግባት በአፍሪካ ምርጡ ብሄራዊ ቡድን የሚል ስያሜ ያገኘውን ሞሮኮን የማሸነፍ ጠንካራ ፈተና ይጠብቃታል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ምሽት አራት ሰዓት ላይ ደቡብ አፍሪካ ከካሜሮን በአል መዲና ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።


 

ደቡብ አፍሪካ በምድብ ሁለት በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በምድብ ስድስት የነበረችው ካሜሮን በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ 16ቱን ተቀላቅላች።

ሀገራቱ በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ1996 ባዘጋጀችው 20ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ፊሊሞን ማሲንጋ፣ ማርክ ዊሊያምስ እና ጆን ሌሲባ ሞሾዩ ግቦችን አስቆጥረዋል።

በሁሉም ውድድሮች ባደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ደቡብ አፍሪካ አምስት ጊዜ ስታሸንፍ አምስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

ደቡብ አፍሪካ አንድ ጊዜ፣ ካሜሮን አምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አሸንፈዋል። 

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በምድባቸው ጥሩ ብቃት ያሳዩት ሀገራት የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። 

የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው የሚጫወቱ ይሆናል።

ትናንት በተደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሴኔጋል እና ማሊ ለሩብ ፍጻሜ አልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም