የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለማረጋገጥ ስርዓታዊና ተቋማዊ አቅም ማጠናከር ይገባል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለማረጋገጥ ስርዓታዊና ተቋማዊ አቅም ማጠናከር ይገባል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦ የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለማረጋገጥ ስርዓታዊና ተቋማዊ አቅም ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ''በመደመር መንግስት ዕይታ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት እመርታ'' በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ወዲህ የመጀመሪያውን ስብሰባ አካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአንድ ሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ የራሱን ችግር በራሱ የመፍትሔ መንገድ እልባት የሚሰጥበትን አቅም ሲገነባ ነው።
በየትኛውም ዓለም የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት እንደ የሀገራቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ስልጣኔ አቅም እንደሚወሰን ገልጸዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር ሥራ ከብሔራዊ ደኅንነት፣ከማህበራዊ ፍትሕ፣ ከሰብዓዊ መብቶች፣ ከሰላም ግንባታና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በጥብቅ ቁርኝት የተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የአደጋ ስጋት አመራር ሥርዓት አስተማማኝነት ለመገንባት ሁሉም የአስተዳደር እርከን፣ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተጋግዘውና ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም፤ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።
በራስ አቅም ሰብዓዊ ድጋፍን ለማሟላት በተቀናጀ የአመራር ሥርዓት ስኬቶችም የብዝኅ ዘርፍ ኢኮኖሚ ተጨባጭ ውጤቶች ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ የመረዳዳት ዕሴት በማጎልበትና የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የምክር ቤቱ መቋቋም ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ተነሳሽነትና የመደጋገፍ ባህል ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ የምክር ቤቱ መቋቋም ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመሸፈን የሚከናወኑ ተግባራትን ለማላቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸኃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ምክር ቤቱ ግልጽ የአሰራር ሥርዓትን በመፍጠር የሰብዓዊ ድጋፍ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ምክር-ቤት ሰብሳቢ አማረ አረጋዊ፤ የኢትዮጵያን በራስ አቅም የአደጋ ጊዜ ምላሽ አጣጥ ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙኅን ገንቢ ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በሰጡት ማጠቃለያ፤ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት በታላቅ የአርበኝነት መንፈስ ለጋራ ስኬት በትጋት መስራት እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
የሰላም ግንባታ፣የልማት ፕሮጀክቶችንና የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችን በማስተሳሰር የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ማሟላት የሚያስችል ስርዓታዊና ተቋማዊ አቅም ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።