ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬት ገንቢ ሚና ይወጣል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ቴሌኮም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬት ገንቢ ሚና እንደሚወጣ የኢትዮ-ቴሌኮም ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሰር ታሪኩ ደምሴ  ገለጹ።    

ኢትዮ ቴሌኮም 130ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በማስመልከት ያዘጋጀውን ሁለት ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪና ሽልማቶች ለአሸናፊ ደንበኞቹ አስረክቧል፡፡

ኩባንያው በሽልማት መርሃ-ግብሩ ላይ ተጨማሪ ስድስት ዘመናዊ መኪኖችን የሽልማት ዕጣዎችን የማውጣት ሥነ-ሥርዓት አከናውኗል፡፡


 

ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ የሽልማት መርሃ-ግብር ከዚህ ቀደም አራት የኤሌክትሪክ መኪኖችን እንዲሁም 13 ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን ለባለ ዕድለኛ ደንበኞቹ ማስረከቡን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም 372 ዘመናዊ ስማርት ስልኮችንና የቴሌብር ኤሌክትሮኒክስ ገንዘብን ጨምሮ በሽልማት መርሐ ግብሩ ከ127 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ አጠቃላይ ዋጋ ያላቸውን ሽልማቶች ሰጥቷል።

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሰር ታሪኩ ደምሴ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የጀመራቸውን ሰፋፊ ስራዎች አጠናክሮ በማጠናከር የበኩሉን ገንቢ ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮ 130 ሜጋ ፕሮሞ እና ኢትዮ 131 ላኪ ስሎት ሽልማት ላይ እድለኛ የሆኑት አሸናፊዎች በሽልማቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ካነጋገርናቸው ባለእድለኞች  መካከል  ከጅማ ከተማ የመጡት ጥንዶች  በጅማ ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኛ የሆነው  ሳሙኤል ጣፋ እና ባለቤቱ ኢሌኒ ለማ ሽልማቱ ድርብ ደስታን እንደፈጠረላቸው ይገልጻሉ፡፡

 

ሌላው ባለ እድለኛ ገብረ ህይወት ታምር በበኩሉ ኢትዮቴሌኮም የኢትዮ 130 ሜጋ ፕሮሞ እና ኢትዮ 131 ላኪ ስሎት ሽልማት  ዕድለኛ በመሆኑ መደሰቱን ተናግሯል፡፡ 

 

ኩባንያው በቀጣይም ደንበኞቹን ተሸላሚ የሚያደርገውን ቴሌ ፕለይ የተሰኘ የሽልማት መርሐ ግብሩን እንደሚያስቀጥልም ተገልጿል።

በዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ተወካዮች፣ የሚዲያ አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም