በመዲናዋ የመደመር መንግስት ዕይታ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈጣን የምርታማነት ዕድገት የላቀ ሚና አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የመደመር መንግስት ዕይታ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈጣን የምርታማነት ዕድገት የላቀ ሚና አበርክቷል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ የመደመር መንግስት ዕይታ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈጣን የምርታማነት ዕድገት የላቀ ሚና ማበርከቱን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመደመር እሳቤ ለመዲናዋ የኢንዱስትሪ ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት ለዘርፉ ዕድገት መፋጠን የላቀ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በለውጡ ማግስት የአዲስ አበባ ከተማን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርታማነት ለማሻሻል የተከናወኑ የፖሊሲና ስትራቴጂ የለውጥ እርምጃዎች የዘርፉን ማነቆ መፍትሔ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የተወሰዱ አሰራር የማሻሻያ እርምጃዎች የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማሳደግ በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚያበረክተውን ድርሻ ከፍተኛ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም የመደመር እሳቤ በተግባር የታየበት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እመርታ በማስመዝገብ ለዘርፉ ዕድገት መፋጠን የላቀ ሚና እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
የመደመር እሳቤን ተከትሎም በመዲናዋ ከ290 በላይ የቦታ ጥያቄዎችን መልስ በመስጠት የአዲስ አበባን የኢንዱስትሪ ቁጥር ወደ 3 ሺህ 824 ከፍ ማድረግ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
አስተዳደሩ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርታማነት የሰጠው ትኩረት ለወጪና ተኪ ምርቶች ጥራትና መጠን ማደግ ጉልህ ድርሻ በማበርከት ለበርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
የማዕድንና ግብርና ዘርፎች የግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ዕድገት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ እመርታ ትርጉም ያለው መፍትሔ መስጠት እያስቻለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በቀጣይም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግና ተኪ ምርቶችን በስፋት ለማምረት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።