ቀጥታ፡

የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር አማራጭ ቅንጦት ሳይሆን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገር ሉዓላዊነት የማስከበሪያ መሠረት ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2017(ኢዜአ)፦ የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር አማራጭ ቅንጦት ሳይሆን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገር ሉዓላዊነት የማስከበሪያ መሠረት መሆኑን የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

“የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ስፔክትረም ልዕልና ለሀገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነ የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር አውደ ጥናት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና መስሪያ ቤት ዛሬ ተካሂዷል፡፡


 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኤሌክትሮኒክ ዋርፌር አማራጭ ቅንጦት ሳይሆን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገራት ሉዓላዊነት መሠረት ነው።

በዚህ ዘመን የሀገራት ኃይል መገለጫዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀያየሩ የመጡበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር በመሬት፣ በባሕር፣ በአየርና በሕዋ ክልል ውስጥ በሚደረጉ ፍልሚያዎች ብቻ ይጠቀሙ እንደነበረም ገልጸዋል።

ዛሬ ዘመናዊ ውጊያ የሚካሄደው በማይታይ እና የጦርነቱን ዕጣ ፈንታ በሚወስን ረቂቅ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ስፔክትረም ምህዳር ውስጥ መሆኑንም አብራርተዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ስፔክትረምን መጠቀም የደህንነት ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገራችን ሰፊ የቆዳ ስፋት እና ተለዋዋጭ ቀጣናዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ ካለን ተጨባጭ የመከላከል አቅም ጋር መጣጣም ይኖርበታል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው፤ የዘመኑ ጂኦ ፖለቲካዊ ፉክክር መልክ እየቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሀገር ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በመሬት፣ በባህር፣ በአየር፣ በሕዋ ወይም በሳይበር ላይ በሚደረግ ተጋድሎ ብቻ ያለመሆኑን አመልክተው፤ በማይዳሰስና በረቂቁ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ስፔክትረም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ዛሬ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ይህንን የፉክክር ዘርፍ በብቃት ለመረዳትና በስፔክትረሙ ላይ አስተማማኝ የበላይነትን ለመጨበጥ የሚያስችል ብሔራዊ አቅም ለመገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለሚገጥሟት ዘመናዊ የጸጥታ ስጋቶች የምትሰጠው ምላሽ በሳይንሳዊ ትንታኔ እና በተቋማዊ ቅንጅት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የተቋማት አመራር ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በየተቋማቱ የሚገኙ እምቅ አቅሞችን መደመርና ቅንጅት መፍጠር ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል።


 

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የሀገራት ደህንነት የሚረጋገጠው መረጃን ቀድሞ የማግኘት፣ ስፔክትረሙን የመቆጣጠርና ጠላት እንዳይጠቀምበት የማድረግ የቴክኖሎጂ የበላይነትን በመያዝ ነው።

ይህንን ምህዳር የተቆጣጠረ ወገን መረጃን ቀድሞ የማግኘት፣ ውሳኔን በፍጥነት የመወሰንና የድል ልዕልናን የመያዝ ስትራቴጂካዊ ብልጫ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር ታሪካዊ ዳራ፣ አሁናዊ የሀገራት ተሞክሮ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወቅታዊና መጻኢ ሁኔታዎችን የዳሰሰ መነሻ ጽሁፍ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡


 

በአውደ ጥናቱ ላይ የተለያዩ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፣ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ በመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ዶክተር አሸናፊ ኦሊ፣ እንዲሁም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለማርያም በፓናሊስትነት ተሳትፈዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ በዋናነት የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ስፔክትረምን በአግባቡ በመቆጣጠርና በመምራት የኢትዮጵያን አሁናዊና መጻኢ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዘርፉን የሚመራ ተቋም መገንባት፣ በዘርፉ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮችን ማላቅ፣ እንዲሁም በባለድርሻ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብርና ቅንጅት ይበልጥ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም