የጉጂ ዞን ቡሳ ጎኖፋ በችግር ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በ12 ወረዳዎች የሰብል ልማት ስራ እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጉጂ ዞን ቡሳ ጎኖፋ በችግር ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በ12 ወረዳዎች የሰብል ልማት ስራ እያከናወነ ነው
አዶላ፣ ታህሳስ 25/2018 (ኢዜአ)፡- የጉጂ ዞን ቡሳ ጎኖፋ በችግር ጊዜ ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅሙን ለማጠናከር በ12 ወረዳዎች የሰብል ልማት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በችግር ጊዜ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ የዞኑ የቡሳ ጎኖፋ ሀላፊ አቶ አባይነህ ሸርቂቻ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዞኑ ለችግሮች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም የማካበት ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው በተለይም የምርት አቅምን የማሳደግ እራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት በምርት ዘመኑ በዞኑ በ12 ወረዳዎች የተለያዩ ሰብሎች እየለሙ መሆኑን ገልጸው ለምርት ማከማቻም በ58 ሚሊዮን ብር ሰባት የማከማቻ መጋዘኖች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ከምርት በተጨማሪ ከዞኑ የቡሳ ጎኖፋ አባላት እስካሁን ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ሀብት ለማሰባሰብ አቅምና አጋዥ የሚሆኑ አሁን ላይ ከ713 ሺህ በላይ አባላት ያሉት መሆኑን ገልጸው በምርትም ይሁን በገንዘብ አቅምን የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዞኑን ህዝብ በማስተባበር ዘንድሮ ለ260 ሺህ 87 ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ያሉት ሃላፊው በቡሳ ጎኖ አቅም ሀብት በማሰባሰብ ሁለንተናዊ ተደራሽ ለመሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ደስታ ገብረየስ፤ በዞኑ ያልማና ሊለማ የሚችል ሰፊ የወል መሬት መኖሩን ጠቁመው በዘመናዊ ግብርና በመታገዝ በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንሰራለን ብለዋል።
በመሆኑም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣትና ለችግሮች በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።