የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን እንገኛለን- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን እንገኛለን- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 25/2018 (ኢዜአ)፦የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ዛሬ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ውይይት ላይ የተሳተፉት ተቋማት በለውጥ አስተሳሰብ የተካተቱና የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉም የተካተቱበት በመሆኑ፣ በጋራ ከምናከናውናቸው ስራዎች በተጨማሪ በየተቋሞቻቸው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት በምናደርገው ርብርብ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
አዲሱ ምክር ቤት በአዲሱ ፖሊሲ፣ አዋጅ እና የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ላይ በመመስረት፤ የሕዝብን አቅም በማስተባበር የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባትና የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ጉዳት በቀነሰ መልኩ ለመከላከል በትጋት ይሠራል።
የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት ስርዓታዊና ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባም በስብሰባችን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል።
ከ2016 ክረምት ጀምሮ በተቀረጹ ፍኖተ-ካርታዎች መሠረት ልመናና ተረጂነትን በምርታማነት ለመተካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ፤ ውጤትም እየተመዘገበ ይገኛል።
በዘላቂነት አስተማማኝ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ መገንባት፣ የመጠባበቂያ ክምችትን በፌደራልና በክልሎች ማደራጀትና ተፈናቃይ ዜጎቻችን በዘላቂነት ተቋቁመው ወደ አምራችነት እንዲመለሱ ማድረግ የመንግሥታችን ዋነኛ ግብ ነው።
በተለይም የማኀበረሰባችንን የመደጋገፍ መልካም ልምምድ እና የአጋርነት እሴት በማጎልበት በየአካባቢያችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የምናደርገው ርብርብ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ጉዟችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዕውቀትና በጥበብ መሻገርን ይጠይቃል። ይህንንም በመደመር ዕይታና በጠንካራ አመራር ለማሳካት ከስምምነት ላይ ደርሰናል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደ ሀገር መላውን ማህበረሰብ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።