የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማዕድን ሃብት ላይ እመርታዊ ስኬት አምጥቷል - ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማዕድን ሃብት ላይ እመርታዊ ስኬት አምጥቷል - ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማዕድን ሃብት ልማት ላይ እመርታዊ ስኬት ማምጣቱን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ገለጹ።
ከጥቂት ወራቶች በኋላ ከውጭ የሚገባን የሴራሚክ ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ እንደሚተካ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ቡልጋ ከተማ አስተዳደር ከውጭ የሚገባን የሴራሚክ ምርት በሀገር ውስጥ የመተካት አቅም የሚኖረው የባጀአ ሴራሚክ ፋብሪካ ተጎብኝቷል።
በዚሁ ወቅት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፤ የባጀአ ሴራሚክ ፋብሪካ ኢትዮጵያን በወለልና ግድግዳ ንጣፍ ምርት ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ሀገር ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የባጀአ ሴራሚክ ፋብሪካ በሁለት የቻይና አልሚ ባለሃብቶች በ10 ቢሊዮን ብር በተሻለ የግንባታ ፍጥነት ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሴራሚክ ፋብሪካው የሚጠቀመው 95 በመቶ ግብዓት ከሀገር ውስጥ መሆንም ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ማንሰራራት ወርቃማ ዕድል መሆኑን አንስተዋል።
የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ኢትዮጵያ በማዕድን ሃብት ያላትን ዕምቅ አቅም በማልማት ተጠቃሚ እያደረጋት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የማዕድን ዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።
ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ማምረት የሚገባው የባጀአ ሴራሚክ ፋብሪካም በመጀመሪያ ዙር በቀን 35 ሺህ ካሬ ሜትር ሴራሚክ እንደሚያመርት አስረድተዋል።
ዜጎችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ በማድረግና የሀገር ውስጥ የሴራሚክ ፍላጎትን በማሟላት ለውጭ ገበያ ጭምር የማቅረብ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
የማዕድን ዘርፍ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰሶ መደረጉም የዘርፉን እመርታ በማሻሻል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ ደረጃ እየሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያን የቤት ልማትና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግራናይትና ማርብል የግብዓት አቅርቦት የሚያሟሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች እየተገነቡ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።