ቀጥታ፡

የግብይት ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦ የግብይት ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሚኒስትሩ የተመራ የልዑክ ቡድን በከተማዋ ተዘዋውሮ የንግድ እንቅስቃሴ ቅኝት አድርጓል።


 

በዚሁ ጊዜ ተቋማቸው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

የወጪ ንግድ ኮንትራትና የፍቃድ አሰጣጡን ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል ሥርዓት መቀየሩን ገልጸው፣ የዲጂታል ግብይት እንዲሳለጥም ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በአንድ ወር ብቻ ጤፍ በዘመን ገበያ የ53 ሚሊዮን ብር ግብይት መፈጸሙን አንስተዋል።

መንግስት የዲጂታል ግብይትን ለማሳለጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ወደ ዲጂታል ግብይት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በቁም እንሰሳት ንግድ ላይ የደላላ ጣልቃገብነት በመቀነስና አሰራሩን በማዘመን የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።


 

የቁም እንስሳት የግብይት ማዕከላትን በማስፋት የግብይቱን ሥርዓት ግልጽና ዘመናዊ መደረጉን ገልጸው፤ከቁም እንስሳት ወጪ ንግዱ ገቢ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከቁም እንስሳት ወጪ ንግድ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው የተናገሩት።

በ2018 በጀት ዓመት ከቁም እንስሳት ወጪ ንግድ 70 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም