ቀጥታ፡

በክልሉ በዲጂታል አሰራር የተደገፉ አገልግሎቶችን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

አርባ ምንጭ፤ታህሳስ 25/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዲጂታል አሰራር የተደገፉ አገልግሎቶችን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መደረጉ ተገለጸ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በክልሉ ዲጂታል 2030ን በማሳካት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።


 

''ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጭ የሚታሰብ መንግስታዊ አገልግሎት አይኖርም'' ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ወረቀት አልባ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ህዝቡን ከእንግልትና ከአላስፈላጊ ወጪ ለማዳን በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ከሁሉም በላይ በክልሉ በዲጂታል አሰራር የተደገፉ አገልግሎቶችን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።

የፋይዳ መታወቂያ ዜጎችን ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር ህይወትን በእጅጉ የሚያቀል በመሆኑ ዜጎች የዚሁ ትሩፋት ተጠቃሚ ለመሆን ፋይዳ መታወቂያ መያዝ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ለማሳካት በተደረጉ ጥረቶች ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የተጀመሩ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እና የዲጂታል መታወቂያ ስራዎች ጉልህ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ዕቅድ ለማሳካት ክልሉ ድርሻውን እንዲጫወት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የክልልና የዞኖች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም