በአማራ ክልል የዘላቂ ሰላምና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የዘላቂ ሰላምና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ባህር ዳር፤ ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የዘላቂ ሰላምና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአስተዳደር ክላስተር የስድስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ሰላምን ከማስፈን ባለፈ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የክልሉን ሰላም ለማወክ የተንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን በመከታተል ጠንካራ ህግ የማስከበር ስራ መሰራቱን አንስተው፥ የሰላምን መንገድ ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችንም መልሶ በማቋቋም ወደ ልማት ስራ እንዲገቡ ተደርገል ብለዋል።
በክልሉ በተለይም በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን፣የዲጅታል አሰራርን የማስፋትና በሁሉም ዘርፎች የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ መደረጉን ገልጸዋል።
በመሆኑም በክልሉ የዘላቂ ሰላም ግንባታን የሚያስቀጥሉና የህዝብን ተጠቃሚነት እውን የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።
በቀጣይም በአስተዳደር ክላስተር ክንውን የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ በማጠናከር ለክልሉ ሰላም፣ ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት በላቀ ቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላም በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከህግ ማስከበር ስራው በተጓዳኝ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን የመልሶ ማቋቋምና ወደ ልማት የማስገባት ስራም መከናወኑን አንስተዋል።
ከአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፍሃድ) ጋር የተደረሰውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተከትሎ ከተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እያስረከቡ በሰላም መግባታቸውንና አሁንም በመግባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ ብርሃኑ ጎሽም በበኩላቸው፤ በክልሉ የፍትህ ስርዓቱን የማዘመንና ተደራሽነቱን የማስፋት ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በፍጥነትና በጥራት መዝገቦች ተጣርተው ክስ በመመሰረት ውሳኔ እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን አሰራርን የሚያሻሽሉ ደንቦችና መመሪያዎችን በማዘጋጀትም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል።
በመድረኩ በክላስተሩ የተካተቱ የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ የስድስት ወሩን ዕቅድ አፈፃፀም በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡ ይሆናል።