ቀጥታ፡

በከተሞች ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ የዲጂታል አገልግሎቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሆሳዕና ፤ ታህሳስ 25/2018 (ኢዜአ) ፡- በከተሞች ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ የዲጂታል አገልግሎቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላከተ፡፡

የቢሮ ኃላፊዎቹ እንደገለፁት፤ በከተሞች ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ የዲጂታል  አገልግሎቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማደራጀት ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው፡፡

የመደመር መንግሥት እይታን በመተግበር ዜጎች ባሉበት ሆነው በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ስማርት ከተሞችን መፍጠር ላይ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ዘጠኝ ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ፈጣንና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም ተግባሩን በማስፋት በ15 ከተሞች ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ሰለሞን በበኩላቸው በከተሞች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል።

በተለይም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ብልሹ አሰራሮችን ለማረምና የተገልጋይ እርካታን ለመጨመር መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡

አገልግሎቱን ለማስፋትም  የመቶ ቀናት እቅድ  መዘጋጀቱንም  ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የመንግሥት አገልግሎትን የተቀላጠፈ ለማድረግ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሰመራ ከተማ መጀመሩን የገለፁት ደግሞ የአፋር ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ጎቦኦ መሀመድ ናቸው። 


 

በዚህም ቀደም ሲል በከተማ አገልግሎት አሰጣጥ  የነበሩ  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቀነስ መቻሉን አንስተዋል።

አገልግሎቱን በማስፋትም በክልሉ አዋሽን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ተደራሽ በማድረግ ተገልጋዩን ለማርካት መታቀዱን   ገልፀዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው መንግሥት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሪፎርሞች መተግበሩን ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ መዘመንም የማህበረሰቡን እንግልት ለመቅረፍ የተጀመረዉ ጥረት አካል መሆኑን  ጠቁመዋል።

ለዚህም በዲጂታል የታገዘ አገልግሎትን እስከ ቀበሌ መዋቅር በማስፋት በዘርፉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የገጠር ትራንስፎርሜሽንን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ማካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም