ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ እያደረገ ነው

ሐረር ፤ታህሳስ 25/2018 ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ እያደረገ መሆኑ ተመላከተ።

በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የ2018 በጀት ዓመት የአገልግሎት እድሳትና ምዝገባ ማስጀመሪያ የንቅናቄ መርሃ ግብር ተከናውኗል።


 

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለም እንዳሉት በአገሪቱ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባለፉት 10 ዓመታት በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የዜጎችን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራ እየተተገበረ ይገኛል።

በክልሉ የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው አገልግሎቱን በማዘመን ረገድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የጤና መድህን አገልግሎት ዘላቂና ቀጣይ እንዲሆን ለማስቻል ከአባላት የተናጠል ድጎማ ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ ሌሎች ዘዴዎችን ተጠቅሞ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ገቢን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን መክረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማዘመንና ዲጂታላይዝድ በማድረግ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የክሊኒክ ኦዲት ስራን  አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በበኩላቸው በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ከ33 ሺህ በላይ የቤተሰብ መሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።


 

በ2018 በጀት ዓመት ከ46 ሺህ በላይ  የቤተሰብ መሪዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ታቅፈው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም ለተመረጡና መክፈል ለማይችሉ 7 ሺህ 478 የአባልነት መዋጮ በክልሉ መንግስት ሙሉ ለሙሉ የሚፈጸም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ  በርካታ  ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ፤ ይህን ስራ ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም አስተዋጽኦውን እንዲያጎለብት ጠይቀዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የወረዳ አመራር አባላት፣ የጤና ባለሙያዎችና ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም