ቀጥታ፡

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍትን ወደ ላቀ የዲጂታል ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሦስት ታላላቅ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍትን ወደ ላቀ የዲጂታል ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሦስት ታላላቅ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች ዛሬ በይፋ የማስጀመር ተግባር ተከናውኗል።

ይህንንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በመገኘት የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች፥ አቤቤ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በመዲናዋ የንባብና የምርምር ባህል ማዕከል ሆኖ ስራ ከጀመረ አራት ዓመታት መቆጠራቸውን ገልጸዋል።


 

ዛሬ በቤተ-መጻሕፍቱ በመገኘትም፥ ተቋሙን ወደ ላቀ የዲጂታል ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሦስት ታላላቅ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን በይፋ ማስጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በዓመት በአማካይ ለ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን አንባቢዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን ይህንን ተቋም ይበልጥ ለማዘመን የሚያስችሉ፦ የተቀናጀ የቤተ-መጻሕፍት አስተዳደር ሥርዓት፣ ዘመናዊ የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት እና ዓለም አቀፍ የምርምር መድረክ (Research Portal) በይፋ ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን አመልክተዋል።

አገልግሎቶቹ አብርሆት በአዲስ አበባ ብቻ የተገደበ እንዳይሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ የተናገሩት ከንቲባዋ ማንኛውም ተማሪም ሆነ ተመራማሪ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ሆኖ የአብርሆትን የዕውቀት ማዕድ መቋደስ እንዲችል ያደርጋሉ ነው ያሉት።

በተጨማሪም የታሪክ ሰነዶችን በዲጂታል መንገድ ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ትልቅ እገዛ እንደሚኖራቸውም አክለዋል።

ከንቲባዋ ቴክኖሎጂዎቹን በማልማት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም