የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው ውድድር ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ከ24ቱ ሀገራት 16ቱ በሞሮኮ ሲቆዩ ስምንቱ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
በምድብ በተደረጉ 24 ጨዋታዎች 87 ግቦች መቆጠራቸውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል። በየጨዋታዎቹ በአማካይ ከሶስት ግቦች በላይ ተቆጥረዋል።
ጨዋታዎቹ በጎል የተንበሸበሹ እና ማራኪ እንቅስቃሴ የተደረገባቸው ናቸው።
የሞሮኮው አዩብ ኤል ካቢ ኮሞሮስ እና ዛምቢያ ላይ በመቀስ ምት ካስቆጠራቸው ድንቅ ግቦች አንስቶ የኮትዲቯሩ አማድ ዲያሉ ካሜሮን ላይ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ከመረብ ላይ እስካገናኛት ግሩም ጎል በርካታ ማራኪ ጎሎችን በምድብ ጨዋታዎች ለመመልከት ተችሏል።
አይኖች ሁሉ ወደ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ባማተሩበት ወቅት ሌላኛው ትኩረት የሳበው ጉዳይ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ጉዳይ ነው።
የሞሮኮዎቹ አዩብ ኤል ካቢ እና ብራሂም ዲያዝ እንዲሁም የአልጄሪያው ሪያድ ማህሬዝ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነቱን በጋራ እየመሩ ይገኛሉ።
12 ተጫዋቾች በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ይከተላሉ።
ናይጄሪያውያኑ አዴሞላ ሉክማን እና ራፋኤል ኦንዬዲካ፣ የሴኔጋሎቹ ኒኮላስ ጃክሰን እና ቼሪፍ ንዳዬ፣ የግብጹ መሐመድ ሳላህ፣ ደቡብ አፍሪካውያኑ ላይል ፎስተር እና ኦስዊን ፍሊፕስ፣ የኮትዲቯሩ አማድ ዲያሎ፣ የአልጄሪያው ኢብራሂም ማዛ፣ የቱኒዚያው ኤሊያስ አቹሪ፣ የማሊው ላሲን ሲናዮኮ እና የሞዛምቢኩ ጌኒ ካታሞ በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት የናይጄሪያው አዴሞላ ሉክማን እና የደቡብ አፍሪካው ላይል ፎስተር በተመሳሳይ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችተው አቀብለዋል።
የኮከብ ግብ አግቢ ማን ይሆናል? የሚለው ጉዳይ በቀጣይ የውድድሩ ጎዞ ምላሽ ያገኛል።