ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ እንሆናለን - ወጣቶች

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የዲፕሎማሲ ክንውኖች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታዎቃል።

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የረጅም ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድን፣ የትውልድንና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምን ባገናዘበ መልኩ ምላሽ የሚያገኝበት የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት አጀንዳ ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ማስገንዘብ ያስቻሉ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ጥያቄው እንዴት ይፈጸም ወደሚል ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ወዳለው ምዕራፍ መሸጋገሩንም አስረድተዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች እንደገለጹት፤ የባህር በር ባለቤትነትን ጨምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ።

አስተያየት ከሰጡት መካከል ወጣት ንጉሤ ወርቁ እንደተናገረው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የሀገሪቷ የህልውና እና የወደፊት ብሩህ ተስፋ መሠረት ነው።

ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክና ሰፊ ህዝብ ያላት ሀገር ብትሆንም፣ የባህር በር ማጣቷ በኢኮኖሚዋና በሉዓላዊነቷ ላይ ተግዳሮት መደቀኑን ተናግሯል።

ይህንን ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ ወጣቶች ግንባር ቀደም ተዋናዮች መሆን ይጠበቅብናል ብሏል።

ወጣት አብዱ ዲንቁ በበኩሉ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተራ የመሻት ወይም የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ህልውና የሚወሰንበት መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብሏል።

ስለሆነም በዓለም አቀፍ መድረኮችና በማህበራዊ የትስስር ገጾች የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊነት ለዓለም ለማስገንዘብ እንደሚሰራ ገልጿል።

ይህ ፍትሀዊ ጥያቄ የጎረቤት ሀገራትን ጥቅም በማይነካ መልኩ በጋራ ልማትና በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ ሊሳካ እንደሚገባ አንስቷል።

ወጣት ዮሴፍ አበራ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን የሚወስን ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ተናግሯል። 

በሰላም፣ በንግግርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከግብ በማድረስ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም