በአዲስ አበባ የተገነቡ የመሠረተ ልማትና የመዝናኛ ስፍራዎችን የመንከባከብ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የተገነቡ የመሠረተ ልማትና የመዝናኛ ስፍራዎችን የመንከባከብ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችንና የመዝናኛ ስፍራዎችን የመንከባከብ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር፣ወንዝ ዳርቻና በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የተገነቡ የመሰረተ ልማት ተግባራት ለነዋሪዎች ምቹ ስነ ምህዳር በመፍጠር መዲናዋን ውበት እያላበሷት ይገኛል።
የመዲናዋ የመሠረተ ልማትና የመዝናኛ ሥፍራዎችን በመንከባከብ ለትውልድ እንዲተላለፉ ማስቻል የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆኑ አያጠያይቅም።
የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ገዛኸኝ ዴሲሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመዲናዋን ዘመናዊነት የሚያስጠብቁ መሠረተ ልማቶችን የመጠበቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማን የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራት መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ጭምር ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በከተማዋ በመንገድ ጽዳት የተሰማሩ ከ10 ሺህ በላይ ሙያተኞች የሚሰበስቡትን ቆሻሻ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ የሽርክና ማኅበር የተደራጁ አካላት መልሰው በመጠቀም ለጽዳትና ውበት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባን ውበትና ጽዳት የመጠበቅ ሥራ መዲናዋን ለቱሪዝም ፍሰትና ለነዋሪዎች እንቅስቃሴ ምቹ ምህዳር በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም በመዲናዋ የተገነቡ የመሠረተ ልማትና የመዝናኛ ሥፍራዎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ተግባር በልዩ ትኩረት መከናወኑ ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል።
በቀጣይም አዲስ አበባን ምርጥ የአፍሪካ መዲና ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ጽዳትና ውበትን የመጠበቅ ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለማዘን የተከናወኑ የአሰራር ማሻሻያዎችም ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማስቻል ገንቢ ሚና መወጣቱን አስረድተዋል።
ይህም መዲናዋን ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ለተጀመረው ጥረት ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመዲናዋ ነዋሪዎችም የአዲስ አበባን ውበትና ጽዳት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን በመጠበቅና በቆሻሻ አወጋገድ ላይ ገንቢ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።