ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች አምስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፏል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ በ20 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በሊጉ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ስድስት ጊዜ ተጋርቷል። በ24 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

በሊጉ እስከ አሁን ሽንፈት ያላስተናገደው ብቸኛ ክለብ ፋሲል ከነማ ነው።

ፋሲል ከነማ ጨዋታውን ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ከሲዳማ ቡና ይረከባል።  

በሌላኛው መርሃ ግብር አርባምንጭ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን 12 ጨዋታዎችን አከናውኖ ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ በስድስቱ አቻ ወጥቷል። በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።

በሊጉ እስከ አሁን ምንም ድል ያላስመዘገበው ብቸኛው ክለብ አርባምንጭ ከተማ ነው።

በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ቡድኑ በ20 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ሃዋሳ ከተማ ደግሞ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ20 ነጥብ አምስተኛ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዘጠኝ ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጨዋታውን ያደርጋል። 

የ16 የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ18 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ወላይታ ድቻ በ11 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ተገጣሚው ወላይታ ድቻ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፈም።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ25 ነጥብ እየመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም