ቀጥታ፡

የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ዛሬ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይመለሳል።

በታንጀር ስታዲየም ሴኔጋል ከሱዳን ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ሴኔጋል በምድብ አራት በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።

በምድብ አምስት የነበረችው ሱዳን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ በምርጥ ሶስተኝነት 16 ውስጥ ገብታለች።

ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። 

በሌሎች ውድድሮች ላይ ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ሴኔጋል አራት ጊዜ ስታሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። 

ሴኔጋል በጨዋታዎቹ ላይ ስምንት ግቦችን ስታስቆጥር ሱዳን አንድ ጎል ብቻ ከመረብ ላይ አሳርፋለች። 

የአፍሪካ ዋንጫ መስራቿ ሱዳን ለመጀመሪያ ጊዜ ሴኔጋልን ለማሸነፍ ትጫወታለች።

በሌላኛው የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ማሊ ከቱኒዚያ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


 

ማሊ በምድብ አንድ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በምድቧ ያደረጋቻቸውን ሶስት ጨዋታዎች አቻ ወጥታለች።

በምድብ ሶስት ተደልድላ ጨዋታዋን ያደረገችው ቱኒዚያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅለች።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ አራት ጊዜ ተገናኝተዋል። ማሊ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ቱኒዚያ እ.አ.አ በ1994 ባዘጋጀችው 19ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ማሊ ፈርናንድ ኩሊባሊ እና በሞቢዶ ሲዲቤ ግቦች 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ሀገራቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ኮትዲቯር ከሁለት ዓመት በፊት ባዘጋጀችው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው። በምድብ አምስት ተገናኝተው አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ሃምዛ ራፊያ ለቱኒዚያ፣ ላሲን ሲናዮኮ ለማሊ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሲናዮኮ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ለማሊ ብሄራዊ ቡድን እየተጫወተ ይገኛል። 

የዛሬ ጨዋታዎች አሸናፊ ሀገራት በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም