በኢሉባቦር ዞን በ257 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ይከናወናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢሉባቦር ዞን በ257 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ይከናወናሉ
መቱ፤ ታህሳስ 25/2018 (ኢዜአ) ፡-በኢሉባቦር ዞን በበጋው ወቅት የተፋሰስ ልማት በ257 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወኑ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አወል መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ፣ የከርሰ ምድርና ገጸ-ምድር ውሀ ሀብት እንዲጎለብት በማድረጋቸው ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል።
የተከናወኑ የልማት ስራዎችም የተራቆቱ አካባቢዎች ወደ አረንጓዴነት እንዲመለሱ በማድረጋቸው የደን ሽፋኑ መጨመሩን ገልጸዋል።
ተግባሩን በማስቀጠልም ለዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በተለዩ 257 ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናሉ ብለዋል።
ስራውንም ለማሳካት ከ300 ሺህ በላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 131 ሺህ ሔክታር መሬት ለማልማት ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በጎርፍ የተጎዳ መሬት ለምነቱ እንዲመለስ በማድረጉ የአርሶ አደሩ ምርታማነት ማደጉን አስታውሰዋል።
ባለፉት ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስቀጠል በዚህ ዓመት በትጋት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን የዞኑ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
በተቀናጀ የተፋሰስ ስራው ለመሳተፍ ከተዘጋጁ አርሶ አደሮች መካከል የበቾ ወረዳ በኮጂ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዱ ሱጳ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ቀደም ሲል በጎርፍ ይጠረግ የነበረ መሬታቸውን ለምነቱ እንዲመለስ በማድረጉ ምርታማነታቸው ማደጉን አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም የጠፉ ምንጮች መልሰው በማገገማቸው በበጋ ወራት በመስኖ ልማት በመሰማራት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ጠቀሜታን በተግባር በማየታቸው በዘንድሮው ዓመት በሚከናወነው የልማት ስራም በንቃት እንደሚሳተፉ አክለዋል።
ከዚህ ቀደም በተሰሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአካባቢያቸው ልምላሜ በመመለሱና የውሃ አማራጮች በመስፋታቸው ምርታማነታቸው መጨመሩን የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ታሪኩ አየለ ናቸው።
የተፋሰስ ልማቱ የተጎዱ አካባቢዎችን እንዲያገግሙ በማድረጉ ህብረተሰቡን ጭምር በመቀስቀስ በስራው በነቂስ እንዲሳተፉ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።