ቀጥታ፡

የገና ባዛርና ኤግዚቢሽን ምርቶችን በተመጣጠኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል-ሸማቾች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ለገና በዓል የተከፈተው ባዛርና ኤግዚቢሽን የበዓል ምርቶችን በተመጣጠኝ ዋጋ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ሸማቾች ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የገና ባዛርና ኤግዚቢሽን በዛሬው እለት በይፋ ተከፍቷል፡፡ 

ኢዜአ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች በመዘዋወር ሸማቾችንና አቅራቢዎችን ስለ ገበያው ሁኔታ አነጋግሯል፡፡

ከሸማቾች መካከል በለጠ ጎንፋ በሰጡት አስተያየት በባዘርና ኤግዚቢሽኑ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣን ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል ብሏል፡፡


 

በባዘርና ኤግዚቢሽኑ የቀረቡ ምርቶችን ጥራታቸውን የጠበቁ እና ዋጋቸውም ከመደበኛው ገበያ ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ገልጾ፤ ለሸማቾች እፎይታን የሰጠ መሆኑን ነው የተናገረው፡፡

ሌላኛው ሸማች ተመስገን አባይ በበኩሉ፤ የተለያዩ የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ተመልክቻለሁ ብሏል፡፡


 

ዘይትን ጨምሮ ሌሎች የፋጆታ ምርቶች በባዛሩ ይዘው ከቀረቡት መካከል አቶ ጌታሁን ሃይሌ በሰጡት አስተያየት፤ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው የቆዳ ውጤቶችና አልባሳትን አቅራቢ በየነ አሰፋ በበኩላቸው፤ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሽማቾች ከማቅረብ ባሻገር ምርቶቻችንን ለደንበኞች እንድናስተዋውቅ አስችሎናል ብለዋል፡፡



 

በቄርቆስ ክፍለ ከተማ እና አካባቢው የተከፈተውን የገና ባዘርና ኤግዚቪሽን በይፋ የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ሀላፊ ተክሌ በዛብህ፤ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ ሽማቹን ከአምራቹ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ነው ብለዋል፡፡ 

ምርቶች ወደ ከተማዋ በተለያዩ አቅጣጫች እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዋጋቸውም የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ባዛርና ኤግዚቢሽኑ እስከ በዓል ድረስ ተከፍቶ እንደሚቆይ ጠቁመው፤ የህብረተሰቡ ፍላጎት እየታየ የሚቀርበው የምርት መጠን እየጨመረ እንደሚሔድ ተናግረዋል፡፡


 

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ምስክር ነጋሽ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክፍለ ከተማው የገበያ ማዕከላት ፣በባዛርና ኤግዚቢሽን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም