የመደመር መንግሥት ሰው ተኮርነትን የእሳቤዎቹ ምሰሶ በማድረግ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ሰው ተኮርነትን የእሳቤዎቹ ምሰሶ በማድረግ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት ሰው ተኮርነትን የእሳቤዎቹ ምሰሶ በማድረግ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የመደመር መንግሥት በሚመራበት የመደመር እሳቤ ውስጥ የዜጎች ክብር፣ ሰብዓዊነትና የማኅበራዊ እሴቶች መጎልበት የማዕዘን ድንጋይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የሀገር ክብርና ትልቅነት የሚለካው በዜጎች ክብርና ትልቅነት በመሆኑ ማንኛውም የልማትና የፖሊሲ ሥራ ዜጎችን ከድህነት የሚያወጣና ክብራቸውን የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
ይህ የሰው ተኮር ሥራዎች እሳቤ በሀገሪቱ ፖሊሲዎች ውስጥ በግልጽ መንጸባረቁን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የማዕዘን ድንጋይ የዜጎችን ክብርና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በተለያዩ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የዜጎችን ሕይወት በመቀየር ላይ ከሚገኙ ሰው ተኮር ተግባራት መካከል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣ የተስፋ ብርሃን አቅመ ደካሞች የምገባ ማዕከላት መስፋፋት እንዲሁም የነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የሰብዓዊ ክብር ማሳያ ሥራዎች ናቸው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት እየተከናወኑ የሚገኙት የአቅመ ደካሞች ቤት መገንባትና የማደስ ሥራዎች እንዲሁም የክረምት በጎ ፈቃድ የበርካታ ዜጎችን ህይወት በማሻሻል ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን ከተረጂነት ማላቀቅ የሀገርና የሰብዓዊ ክብር ጉዳይ ነው ያሉት ተጠሪ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ አንገቷን ያስደፋውን የልመና እና ተመጽዋችነት አስነዋሪ እሳቤና ድርጊት በዘላቂነት ለማስቀረትም የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ሥራ በፖሊሲ ደረጃ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
በተለያዩ አደጋዎች ለሚፈናቀሉ ዜጎች በሀገር ውስጥ አቅም ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ ቁመና እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም ተቋማዊ አሠራር መዘርጋቱን አስረድተዋል።
ይህም ሰብዓዊ ክብራችንን፣ የሀገር ሉዓላዊነትንና የኢኮኖሚ ነጻነትን በተሟላ ደረጃ ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ ሰብዓዊ ክብራችንን እንዳናስጠብቅ፣ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ በጎ ሥራዎች እንዳይሳኩ እንቅፋት ለመፍጠር የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህ የኢትዮጵያን ክብርና ከፍታ የማይፈልጉ አካላት ግጭት በመቀስቀስ፣ ሰውን በማፈናቀልና በማስራብ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት እንደሚሠሩ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ለሀገር ግንባታና ለዜጎች ክብር በጋራ መቆም እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የመደመር መንግሥት የጀመራቸውን ዜጋ ተኮር የልማትና የሰብዓዊነት ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።