በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች የግብርና ቢሮ አመራሮች ገለጹ።
ሦስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ ሥርዓተ ምግብን የማሻሻል እንዲሁም የዜጎችን የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማሳደግ ዓላማዎች አሉት፡፡
በመርሀግብሩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፣የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እና የሲዳማ ክልል የዘርፉ አመራሮች በመርሀግብሩ የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ተረፈ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በክልሉ በእንስሳትና ዓሣ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃትን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት የተሰማሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑና ምርታቸውንም ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ በክልል ዝርያቸው የተሻሻለ የወተት ላሞች ቁጥር በመጨመሩም በወተት ምርት ላይ ከፍተኛ ዕድገት ማምጣቱን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከአንዲት ላም በቀን የሚገኘው ወተት 1 ነጥብ 5 ሊትር ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው በአሁን ወቅት ዝርያዋ ከተሻሻለ አንዲት ላም በቀን በአማካይ እስከ 15 ሊትር ወተት ለማግኘት ተችሏል ብለዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ከመጀመሩ በፊት በክልሉ በዓመት የሚመረተው የወተት መጠን 321ሚሊየን ሊትር እንደነበር አስታውሰው፣ ዘንድሮ 744 ሚሊዮን ሊትር ወተት ለማምረት መታቀዱንና እስካሁን ድረስ 50 በመቶ የሚሆነው መመረቱን አስረድተዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ በበኩላቸው በክልሉ ህብረተሰቡን በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ በወተት፣ በዶሮ፣ በማር እና ዓሣ ልማት 2ሺህ 785 መንደሮች ተደራጅተዋል ብለዋል፡፡
በነዚህ መንደሮች የዝርያ ማሻሻል፣ የዶሮና ዓሣ ጫጩት እንዲሁም የዘመናዊ ቀፎና ሌሎች አቅርቦቶችን የማሻሻል ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው ምርትና ምርታማነትም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
ለዓብነት መርሀ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት 135 ሚሊዮን የነበረው የዕንቁላል ዓመታዊ ምርት በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ወደ 227 ሚሊዮን ማድረስ እንደተቻለም ጠቅሰዋል፡፡
በዓሣ ሥጋ እንዲሁም በማር ምርትም ምርታማነትና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መቻሉንም አስረድተዋል።
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ፎና በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ከቤተሰብ ብልጽግና ፓኬጆች ጋር በማስተሳሰር ሁሉም ቤተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ቀደም ሲል ከሐይቅና ወንዞች ብቻ ይገኝ የነበረውን ዓሣ አሁን ላይ የውሃ አማራጭ ባለባቸው አካባቢዎች እንዲሁም አርሶ አደር በጓሮው በሚያዘጋጀው አነስተኛ ኩሬ ዓሣ እየተመረተ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የማህበረሰቡ የአመጋገብ ሥርዐት ከመሻሻሉ ባለፈ ገቢውን ለማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።፡
በተያዘው በጀት ዓመት 1ሺህ 500 የዓሣ ኩሬዎች በአርሶ አደሮች ጓሮ የማዘጋጀትና በቂ የዓሣ ጫጩቶችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራው ጎን ለጎን ለእንስሳት እንክብካቤ ትኩረት መሰጠቱን አስታውሰው፣ ለዚህም ሁሉም አርሶ አደር በጓሮው የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ተክሎችን እንዲተክል እየተየደረገ ነው ብለዋል።