ቀጥታ፡

የስማርት አዳማ ፕሮጀክት ግቦችን ለማሳካት ዲጂታል መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ የስማርት አዳማ ፕሮጀክት ግቦችን ለማሳካት ዲጂታል መንግስታዊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት መሰጠቱን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ ገለፁ።

በአዳማ ከተማ ዲጂታል መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማጠናክርና ህብረተሰቡን የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ በወቅቱ እንደገለፁት የስማርት አዳማ ፕሮጀክትን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት አካል የሆነው ፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል።

ይህም የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ በማድረግ ህብረተሰቡ ባለበት ቦታ ሆኖ የመንግስት አገልግሎትን በተቀላጠፈና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማግኘት ያግዛል ብለዋል።

የመንግስት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝድ ማድረግ ተገልጋዩ ከመሬት ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን፣ የገቢ ግብር፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የከተማዋን ፀጥታ በካሜራ በመቆጣጥር ምላሽ መስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።


 

የስማርት ሲቲ አካል የሆነው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሁሉንም አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ በማድረግ በአንድ ቦታ ለማግኘት የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂው ስርአትም ሌብነትና የመሬት ምዝበራን በማስቀረት የከተማዋን ገቢ በማሳደግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዲሳለጡ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በውይይቱ ከተሳተፉ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ሀሰን ጂማ እንደገለፁት የከተማዋ የዲጂታል አገልግሎት ጊዜና ገንዘባቸውን ቆጥቦላቸዋል።

ዲጂታል አገልግሎቱ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር መተሳሰሩ ቀደም ሲል በከተማዋ ይስተዋሉ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ የተሻለ አገልግሎት እንድናገኝ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ በላቸው ደምሴ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም