ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መንግስት ልማትን በዕውቀት ለመምራት ለጀመረው ስራ ተደማሪ ጉልበት ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መንግስት ልማትን በዕውቀት ለመምራት ለጀመረው ስራ ተደማሪ ጉልበት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ75 ዓመታት ለኢትዮጵያ የእውቀት ብርሃን ያበራው የዕውቀት ቤት ነው ብለዋል።

በትጋት የሚመራ ምርምር፣ በሙግት የሚዳብር ሃልዮት፤ በአመክንዮ የሚበለጽግ ፍልስፍና የዩኒቨርሲቲው መለያ ቀለሞች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የዕውቀት ብርሃን መፍለቂያ እና የለውጥ ጥሪ ማስተጋቢያ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ዛሬም የጀመርነውን ልማት በዕውቀት ለመምራት ተደማሪ ጉልበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከምሥረታው ጀምሮ የኢትዮጵያ የለውጥ እና የልማት ጥያቄዎች የፈለቁበት፤ የጊዜው ትንታግ ወጣቶች የለውጥ አብዮት የጎሰሙበት የታሪክም የዕውቀትም ቤት እንደሆነም ነው ያወሱት።

ዛሬም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተደረገው ምክክርም ትናንት እና ዛሬን እንዲሁም ዛሬን እና ነገን፤ ዘላቂ ብልጽግናን ከተሳካ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጋር አሠናስሎ ለመምራት ጉልበት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ተምራችሁ፣ በዕውቀት ተኮትኩታችሁና ካባ ጭናችሁ ዛሬ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ተቋማት ለምታገለግሉ ምሁራንና ባለሞያዎች እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

በተጨማሪም የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት በርትታችሁ እየተማራችሁ ላላችሁ ጥበብ ፈላጊ ተማሪዎች በሙሉ እንኳን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም