በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን
አሶሳ፤ ታህሳስ 24/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን ትኩረት መሰጠቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት፣ በኮደርስ ስልጠናና በሌሎች የልማት ስራዎች ዙሪያ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የነበራቸውን የሥራ ስምሪት በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው።
በክልሉ በከተሞችና በገጠር እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት በማከናወን የከተሞችን ገፅታ ለማሻሻልና ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ከአሶሳ ከተማ በተጨማሪ በባምባሲ፣ ግልገል በለስና ከማሺ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ መጀመሩን ጠቁመው፥ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የአመራሩ ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በየወረዳው የገጠር ኮሪደር ስራ የሚከናወንባቸው ቦታዎች መለየታቸውንና የግንባታ ስራ መጀመሩን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የአካባቢው ማህበረሰብ ለስራው ውጤታማነት ያሳየው ድጋፍና ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።
የ5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠናን በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ ዜጎች ስልጠናውን እንዲወስዱ ተቋማት በተቀናጀ አግባብ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከፍተኛ አመራሮች በሁሉም አካባቢዎች ያደረጓቸው ህዝባዊ ውይይቶች በክልሉ ሠላምን ለማጽናት ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ያመላከተ እንደነበር አስታውቀዋል።