ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
የገናና ጥምቀት በዓላት በደማቁ ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ ጎንደር ናት።
የጥንታዊ ስልጣኔና የበርካታ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነችው ጎንደር አሁን ላይ በኮሪደር ልማት ውበቷ የበለጠ ተገልጿል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ከተማዋ በፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለች ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የጥምቀት በዓልን በጎንደር ያከበረ እንግዳ አሁን ላይ ውበቷ የበለጠ የፈካና የተገለጠዋን ጎንደር ነው የሚያገኘው ብለዋል።
በከተማዋ ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት መንገድ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ማነቃቃቱን ገልጸዋል።
ለ2018 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ሁለት ሚሊዮን ያህል ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ያነሱት አቶ ቻላቸው ለዚህ ደግሞ እንግዳ ተቀባይ የሆነው የጎንደር ህዝብ በጉጉት እየጠበቀ ነው ብለዋል።
ጥምቀትን የመሳሰሉ ክብረ-በዓላት የህዝቡን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፣በዓሉን በጋራ ከማክበር ባለፈ ዘላቂ ወዳጅነት የሚመሰረትበት ነው ብለዋል።
ወደ ከተማዋ የሚመጡ ጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ታሪካዊ ቅርሶችን ከመጠበቅና ከማደስ ባለፈ በተለይም ''ሕይወት በአብያተ መንግስት'' በሚል በዚያ ዘመን የነበሩ ሁነቶችን የሚያሳይ ትዕይንት ተጀምሯል ነው ያሉት።
ይህም በተለያዩ ገዥዎች ዘመን የነበሩ ትዕይንቶች ከጽሁፍ ባለፈ በተግባር ማሳየት የቱሪስቶችን ቆይታ እንዲያራዝም እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ በቀን ብቻ ይከናወን የነበረውን የጉብኝት ጊዜ በምሽትም በማስጀመር ወደ ከተማዋ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ እንግዶች ታሪካዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘም ባለፈ ለከተማዋ ኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ከ400 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውና ተጎድቶ የነበረው የጎንደር የጥምቀት ማክበሪያ ስፍራ፣ በአሁኑ ወቅት ታድሶ አዲስ ገጽታ መላበሱን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልፀዋል።
የጥምቀት ማክበሪያ ቦታውን ዕድሳት ጨምሮ የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት እንግዶች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።