በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት እንዳለው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሰሜን፣ ምስራቅ፣ መካከለኛውና ደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ አገራችን የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ እንደሚቀጥል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።
በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
በሌላ በኩል ከሚጠናከሩ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ላይ በመነሳት በደቡብ ምዕራብ፣ምዕራብ፣ሰሜን ምስራቅና መካከለኛው የአገሪቱ ክፍሎች አልፎ አልፎ በጥቂት ቦታዎች ላይ አነስተኛ ዝናብ እንደሚኖር አስታውቋል።
ዝናብ ሰጪ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ገጽታ እንደሚኖረውም ገልጿል።
በአብዛኛዎቹ የመኸር አብቃይ አካባቢዎች ላይ ደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ የሚጠበቅ ሲሆን በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አስታውቋል።
የሚኖረው የበጋው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ በመከናወን ላይ ለሚገኘው የድህረ ሰብል ስብሰባ ስራዎች አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይጠበቃል ብሏል።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በጥቂት የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙ ጠቁሟል።
የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ በሚገኙ ተፋሰሶች በሚቀጥሉት አስር ቀናት የተሻለ የገጸ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብሏል።
በሌላ በኩል የተቀሩት አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ተፋሰሶች በበጋው ደረቅ የአየር ሁኔታ ተፅዕኖ ስር እንደሚቆዩ ይጠበቃል ሲል ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።