ቀጥታ፡

 የመሬት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የመረጃ አያያዝን ማዘመን ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ 

አርባ ምንጭ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የመረጃ አያያዝን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ፤ በክልሉ የመሬት አስተዳደር ስርአትን በማዘመን ዘርፉ ለክልሉ ዕድገት ያለውን ሚና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምን በመተግበር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም የሀብት ምንጭ የሆነውን መሬት በአግባቡ ማልማት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።


 

የመሬት ሀብትን ከማልማት ባለፈ የመረጃ ስርአቱን በማዘመን የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ  ጋር ማስተሳሰር ማስፈለጉን ጠቁመዋል።

በክልሉ የከተማና የገጠር መሬት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የመሬት መረጃ  አያያዝን ማዘመን ወሳኝና አስገዳጅ መሆኑን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።

የመሬት ሀብት አጠቃቀምን ከማዘመን ጎን ለጎን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራን በማጠናከር የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ በማድረግ ምርታማነትን መጨመር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የገጠር የመሬት አስተዳደር ስርአትን በማዘመን አርሶ አደሮችን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

በክልሉ የከተማ መሬቶችን በኢንቨስትመንት ስም አጥረው የያዙ አካላት ወደ ልማት እንዲገቡ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ  ወደልማት በማይገቡት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምት ይወሰዳል ብለዋል።

በሚቀጥሉት ሦስት ወራት የከተማ መሬት የካዳስተር ስርአትን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ፤ ቢሮው ዘመናዊና ቀልጣፋ የመሬት አስተዳደር ስርአት በመዘርጋት የዜጎች የመሬት አጠቃቀም መብትን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።


 

ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርአትን በመዘርጋት በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ብሎም የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአርሶ አደሮችን የመሬት ሀብት ከዘመናዊ የመረጃ ስርአት ጋር ለማስተሳሰር ለሚከናወኑ ስራዎች ስኬታማነት አርሶ  አደሩ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም