ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት መርሐግብር ተጠቃሚ ሆነናል - የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች

ሻሸመኔ ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት መርሐግብር በወተትና በዶሮ እርባታ ስራ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በሻሸመኔ ከተማ በኢንሼቲቩ እየተሳተፉ የሚገኙ ነዋሪዎች ገለጹ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ  ነዋሪዎች ፤ በሌማት ትሩፋት በወተትና ዶሮ እርባታ በመሰማራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማየታቸውንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ገልጸዋል፡፡

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ገነት ሲሳይ እንዳሉት፤ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን የዶሮ እርባታን ከጀመሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡

500 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማስገባት ወደ ስራው የገቡት ወይዘሮ ገነት በግብርና ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ ታግዘው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በቤታቸው ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ ጎንለጎን በሚሰሩት የዶሮ እርባታ ስራ በቀን ከ400 በላይ እንቁላል እንደሚያገኙና ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ገቢ ማግኛ እንደሆናቸውም ጠቁመዋል።


 

የወተት ላም እርባታን ጨምሮ በተቀናጀ የግብርና ስራ የተሰማሩት አቶ አሊይ ቃባቶ፤ በ50 ዶሮዎች የጀመሩት ስራ አድጎ በቀን እስከ 2 ሺህ እንቁላል ለገበያ ለማቅረብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዶሮ እርባታው ጎን ለጎን የጀመሩት የወተት ላም እርባታም ከ25 ላሞቻቸው በቀን ከ240 ሊትር በላይ ወተት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡


 

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ ሌንጮ መሀመድ (ዶ/ር)፤ በከተማዋ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችል አቅምን እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ በወተትና በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ዜጎችን ከ3 ሺህ 400 በላይ ክላስተሮች በማዳራጀት ዝርያ ማሻሻልን ጨምሮ ድጋፍ እየተሰጠ ሲሆን በዚህም ከ29 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡


 

 የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አዳነ ተክለጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ የዜጎችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም