ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዘርፉ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት የመጣበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዘርፉ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት የመጣበት ነው
ወልዲያ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በዘርፉ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት የመጣበት መሆኑን የኢንፎርሜሽ ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታኅሣሥ 11 ቀን 2018 ዓ.ም የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ይፋ በማድረግ የዲጂታል 2025 ክንውን ደግሞ በስኬት መጠናቀቁን መግለፃቸው ይታወሳል።
በሰሜን ወሎ ዞን ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዘርፉ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት የመጣበት መሆኑን ገልጸዋል።
የአይሲቲ ባለሙያ የሆኑት ታደሰ አብዬ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በዘርፉ ጽኑ መሰረት ያኖረ ስኬታማ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
የስትራቴጂው መተግበር በበርካታ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥና የአሰራር ቅልጥፍናን፣ የቁጥጥርና ተጠያቂነት አሰራርን በማስፈን እንዲሁም ብልሹ አሰራርን መከላከል አስችሏል ብለዋል።
ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በማሳካት የአገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ዳር ለማድረስ መሰረት የጣለ በመሆኑ በጋራ ልንረባረብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የኮሙኒኬሽን ባለሙያው አሰፋ መስፍን፤ በኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት እመርታዊ ለውጥና ማንሰራራት ማምጣቱን ገልጸው ለቀጣዩ እቅድ የላቀ ስኬት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በተለይም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስና ሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን አንስተው በፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ተቋማት የታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሳያነት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ለፍጥነት፣ ፈጠራና ለሀገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ ለ2030 ስትራቴጂክ እቅድ ስኬት ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል።