ቀጥታ፡

አርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው አድጓል

አምቦ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን በምዕራብ ሸዋ ዞን የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በዞኑ  የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደሮች ፤ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በበጋ መስኖ የአትክልት ልማት ላይ በመሰማራት እያመረቱት በሚገኘው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስርዓተ-ምግባቸውን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።


 

አርሶ አደር ገዛኸኝ መኮንን፤ በበጋ ወራት በመስኖ ካለሙት አትክልትና ፍራፍሬ  ለቤተሰባቸው የተመጣጠነ ምግብን ከማቅረብ ባለፈ ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።

የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍን  በመተግባር  ሙዝን በክላስተር እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የወረዳው አርሶአደር ወጣት አብዲሳ ጉደታ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ከመሰማራቱ በፊት ስራ አጥ እንደነበር  በማንሳት አሁን ላይ  በመስኖ ቀይ ሽንኩርት፣ ሙዝና ቲማቲም በማምረት ገቢውን ማሳደጉን  አስረድቷል፡፡


 

በአትክልት ልማት ላይ በመሰማራት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን የተናገሩት ደግሞ  የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ሙልሳ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡


 

በትንሽ መሬት ላይ ወቅትን ሳይጠብቁ በመስኖ በማምረት ተጠቃሚ በመሆናቸው ለሌሎች አርሶ አደሮች ልምዳቸውን ማካፈላቸውን ተናግረዋል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ መንገዱ ጉርሙ ፤ በዞኑ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን  የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም በበጋው ወራት በቀይ ሽንኩርት፣ በድንች፣ በሙዝና በቲማቲም ልማት ሦስት ሺህ 120 ሄክታር መሬት በመሸፈን  646 ሺህ 553 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ  መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በአትክልትና ፍራፍሬዎች ከለማ መሬት እስካሁን 180 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

ለአርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በብዛት እየለሙ ያሉባቸው ወረዳዎች ባኮ፣ ዳኖ፣ ኖኖ፣ ቶኬ ኩታዬ፣ ምዳቀኝ፣ ግንደበረት፣ ሊባን ጃዊ እና ጅባት ወረዳዎች እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም