የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የጋራ ዕድገትን የሚያረጋግጥ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የጋራ ዕድገትን የሚያረጋግጥ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ የጋራ ዕድገትን የሚያረጋግጥ ምክንያታዊና ስትራቴጂካዊ ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ።
የዓለም ኃያላን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚራኩቱበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና፣ በቀይ ባሕር አቅራቢያ የምትገኘው ኢትዮጵያ የበይ ተመልካችነትን የታሪክ ስብራት ለማረም ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ እያደረገች ይገኛል።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው የረጅም ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድን፣ የትውልድንና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ ሲሆን ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ የተከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎችም ውጤት እያስገኙ ነው፡፡
የታሪክና የባሕል ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታሪክና ክብር ከቀይ ባሕርና ከዓባይ ወንዝ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።
ሁለቱም የውኃ አካላት ለኢትዮጵያ ዕድገትና ሥልጣኔ አማራጭ ሳይሆኑ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር የህልውና ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በፊት የታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤት የነበረች ሀገር መሆኗን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ አሁን የሚደረገው ጥረት የታሪክ ስህተትን በማረም የራስን ተፈጥሯዊ ሀብት የማስመለስ ትክክለኛ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ዕድገትና መረጋጋት ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
አሰብ የኢትዮጵያ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር ነው በማለት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በየመን የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ቶፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከራሷ ባሕር በር እንድትርቅ የተደረገበት ሴራ የሚያስቆጭ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለጥያቄው ምላሽ ለማስገኘት እየተከናወነ ያለው የዲፕሎማሲ ተግባር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ጠረፍና ቀይ ባሕር ለዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ያላቸውን ከፍተኛ ፋይዳ ያነሱት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት መረጋገጥ ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ይህን የትውልድ ጥያቄና የብሔራዊ ጥቅም አንኳር ጉዳይ ከግብ ለማድረስ ሁሉም ዜጋ በጋራ ሊቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።