ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬቶች ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሠረት ናቸው

ጅግጅጋ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ በአገልግሎት አሰጣጥና በዜጎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ስኬቶች ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሰረት መሆናቸውን በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ባለሙያ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቀቅያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የተሳካ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል ።

በስትራቴጂው በግብርና፣ በማዕድን ብሎም በኢንዱስትሪው እንደተገኘው ስኬት በዲጂታሉ ዘርፍም መገኘቱን አንስተው ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት ፅኑ መሰረት እንደሚሆነው ማመላከታቸውም እንዲሁ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የአይ ሲ ቲ ዳይሬክቶሬት የኔትወርክ ቡድን መሪ ታደለ ነጋ፤  የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና እድገትን ለማሳካት ጠንካራ መሰረት ያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በተቋማት እና በአገልግሎት አሠጣጥ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገበበት መሆኑንም አክለዋል።

በተለይም የተቋማት የአሠራር ሥርዓት እና ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ለውጦች የተገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

በክፍያ ሥርዓት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና በሌሎችም ሴክተሮች በዲጂታል ዘርፉ በተሠሩ ሥራዎች አበረታች ስኬቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ዜጎች የተለያዩ ወጪዎችን የእጅ ስልካቸውን ተጠቅመው በቀላሉ ክፍያዎችን መፈጸም የሚያስችሉ የሲስተም ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን ጠቅሰዋል።

በጤና ተቋማት ከወረቀት ንክኪ ነጻ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸው ይህም የዜጎችን የጤና መረጃዎች ወደ ዲጂታል ሲስተም በማስገባት እና ጤናቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።

በትምህርት ዘርፉም አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በበይነመረብ መስጠት መቻሉን ገልፀው  ይህም ኩረጃን ማስቀረቱንና ተማሪዎች የተለያዩ ዕድሎችን መጠቀም እንዲችሉ የዲጂታል ማጎልበት ኢንሼቲቭ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በዘርፉ የተገኙት ስኬቶችን መሠረተ በማድረግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ውጤታማነት የዘርፉ ባለሙያዎች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም