ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ በሚያሸጋገር መልኩ ይተገበራል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ በሚያሸጋገር መልኩ ይተገበራል
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 24/2018 (ኢዜአ)፡- ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ በሚያሸጋገር መልኩ እንደሚተገበር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር፣ በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት የስትራቴጂው ቁልፍ ትልሞች መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራዎች ቴክኖሎጂን በስፋት እየተጠቀመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የተለያዩ መተግበሪያዎችን በራስ አቅም በማበልጸግ እንዲሁም ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በፖሊስ ሥራዎች ላይ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ሕብረተሰቡ የወንጀል ጥቆማዎችንና የሚፈልጋቸውን መረጃዎች በአካል ፖሊስ ጣቢያ ሳይገኝ በሞባይል ስልኩ ብቻ የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ኮሚሽነር ጄኔራሉ ገልጸዋል።
አክለውም ከአንድ ወር በኋላ ሰው አልባ የፖሊስ ጣቢያ (Smart Police Station) በአዲስ አበባ ሥራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
የጣት አሻራን አውቶሜት የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የጦር መሣሪያ ምዝገባን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።
ፌደራል ፖሊስ በ2030 የወንጀል ምርመራ፣ መከላከልና የውስጥ አሠራሮችን በቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ለማዘመን በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ፖሊሳዊ አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ የሚያጎለብት መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም 196 ሀገራት የሚሳተፉበት የዓለም አቀፉ ፖሊስ (ኢንተርፖል) ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ተቋሙ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና የዘመነ መሆኑን ለማሳየት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።