ቀጥታ፡

የጉምሩክ አገልግሎትን ለማሳለጥ የሚያስችሉ የሕግ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦ለጉምሩክ አገልግሎትና ለንግድ ሥርዓቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና የዘርፉን ተወዳዳሪነት ማሳደግ የሚያስችሉ የሕግ ማሻሻያዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገለጹ። 

የጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ዋጋ አተማመን መመሪያ ማሻሻያን አስመልክቶ ከአስመጪና ላኪዎች እንዲሁም ከጉምሩክ አስተላላፊዎች ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።


 

በውይይቱ ላይ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ የጉምሩክ ተቋም ለመገንባት በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። 

የንግድ ሥርዓቱን ማሳለጥና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር የሪፎርሙ ዋና ምሰሶ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉ የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ግልጽ፣ ተዓማኒና ፍትሐዊ የጉምሩክ አገልግሎት በመዘርጋት የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል። 

የጉምሩክ ዋጋ አተማመን መመሪያ ማሻሻያ ያስፈለገውም የኢትዮጵያን አሠራር ከዓለም የንግድ ድርጅት የዋጋ አተማመን ስምምነት መርሆዎች ጋር ለማጣጣምና ግልጽነትን ለመፍጠር መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። 

ይህ አዲሱ መመሪያ በጉምሩክ አዋጅ የተደነገጉ መርሆዎችና ድንጋጌዎች በተግባር እንዲተረጎሙ የሚያስችል ግልጽ አሠራር እንደሚዘረጋ ተገልጿል። 

በጥቅሉ ተቋሙን በቴክኖሎጂና በሕግ ማዕቀፍ በማዘመን ለንግዱ ማኅበረሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኝነቱን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም