በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሃገረ መንግስት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ እድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሃገረ መንግስት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ እድል ነው
አሶሳ፤ታህሳስ 24/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሃገረ መንግስት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ እድል መሆኑን የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በአዋጅ ተቋቁሞ ስራ ከጀመረ በኋላ ከዝግጅት እስከ ምክክር ምእራፍ እስካሁን በርካታ ተግባራትን ማከናወን ችሏል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉሙዝ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለሜሳ ኔኖ፥ ሀገራዊ ምክክሩ በምክክር ችግሮችን የመፍታት እድል ይዞ የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሃገረ መንግስት ለመገንባት ታሪካዊ እድል መሆኑንም አክለዋል።
በመሆኑም ይህንን ታሪካዊ እድል በስኬት ለመቋጨት ሁላችንም በምክክር ችግሮችን የመፍታት ቁርጠኝነት ማሳየት አለብን ብለዋል።
በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በመምከርና ለመፍትሄው በመስራት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባለቤት ሊሆኑ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት ፓርቲያቸው እስካሁን የነቃ ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ምክክሩ በስኬት እስከሚጠናቀቅ ድረስ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የጉሙዝ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ለምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ አጀንዳዎችን ማስረከቡን አስታውሰው፥ በጉዳዮች ላይ በመምከር የመፍትሄው አካል ለመሆን መዘጋጀቱን ገልጸዋል።