ቀጥታ፡

በኮምፓክት ፕሮግራም የኤሌክትሪክ ሽፋንን 75 በመቶ ለማድረስ የተያዘው ዕቅድ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ምቹ መደላድል ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በኮምፓክት ፕሮግራም ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋንን 75 በመቶ ለማድረስ የተያዘው ዕቅድ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ታኅሣስ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክትም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽነትን የማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል የመፍጠር፣ የዜጎችና ተቋማትን መተማመን የማጎልበት ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት በአጽንኦት ገልጸዋል።

የሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በማስፋት የዜጎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ በሰው ተኮር ዲጂታል ሥርዓት ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ማስገንዘባቸው ይታወሳል።


 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው እንደ ሀገር የሚፈለገው ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የኃይል አቅርቦት መሠረት ነው ብለዋል።

እያንዳንዱ የዲጂታል አገልግሎት የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢንተርኔት የመንግሥት ዲጂታል አገልግሎት፣ የባንክና የፈጠራ ሥራዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ ዘርፎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ በከተማ ደረጃ 63 በመቶ በገጠር ደግሞ 45 በመቶ ዜጎች የኃይል ተደራሽ ሲሆኑ፤ አጠቃላይ ሀገር አቀፍ ሽፋኑ 54 በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።


 

ባለፉት ዓመታት የኃይል ሽፋኑን ከፍ ለማድረግ በመንግሥትና በውጭ ፋይናንስ አማራጮች የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ዕድገት የሚመጥን የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ከተለመደው አሠራር ውጪ የአተያይ አድማስን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

ለዚህም የዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በሰብ ሰሀራ የሚገኙ 300 ሚሊየን ዜጎችን የኃይል ተደራሽ ለማድረግ ኮምፓክት የተሰኘ ፕሮግራም ተቀርፆ ወደ ተግበራ መግባቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም በዚህ ፕሮግራም መሰረት በ2030 አጠቃላይ የኃይል ሽፋኗን 75 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እየሠራች እንደምትገኝ አስታውቀዋል።


 

ይህም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬታማነት ምቹ መደላደል በመፍጠር የኃይል ተደራሽነቱን ለማስፋት ያስችላል ብለዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጎች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተሳታፊነት ለማረጋገጥ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት ለማስፋት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በትጋት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል። 

በኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለመፍጠር የ25 ዓመት  ማስተር ፕላን ጥናት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ይህም በቀጣይ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ፍላጎትን ማሟላት የሚያስችል አስተማማኝ ኃይል ማቅረብን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።


 

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በከተማ 95 በመቶ በገጠር ደግሞ 90 በመቶ የኃይል ሽፋንን ለማሳደግ ግብ ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም