ቀጥታ፡

በዞኑ የደረሰ ሰብል በቴክኖሎጂ ታግዞ ከብክነት በጸዳ መልኩ ተሰብስቧል

ጎንደር፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅቱ በ532 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል በቴክኖሎጂ ታግዞ ብክነትን በቀነሰ መልኩ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በምርት አሰባሰብ ወቅት ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ለመቀነስ አርሶ አደሩ የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም ተደርጓል።


 

በምርት ዘመኑ በተለያዩ ሰብሎች 550 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን አስታውሰው ምርቱን ለመሰብሰብ በተደረገ ጥረት በ532 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል የምርት ብክነትን በቀነሰ መልኩ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ስለግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አርሶ አደሩ በቂ ስልጠና እንዲያገኝ መደረጉን ጠቁመው፣ ለምርት አሰባሰቡ 3ሺህ 200 የበቆሎ መፈልፈያዎችን ጨምሮ 22 አነስተኛ የሰብል መውቂያ ማሽኖች ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።

የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ትኩረት በመደረጉም በምርት አቀማመጥ ወቅት በነቀዝና በሌሎች ተባዮች ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ከ27 ሺህ በላይ የፕላስቲክ ከረጢት ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።


 

በቤት ውስጥ አይጦች ሊያደርሱ የሚችለውን የምርት ብክነት ለመከላከልም 114 የብረት ጎተራዎች ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ መደረጉን ነው አቶ ንጉሴ ያስታወቁት። 

በምርት ዘመኑ የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን አስታውሰው፣ ለዚህም 240 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም፣ 274 ሺህ ሄክታር በመስመር እና 50 ሺህ ሄክታር መሬት በሜካናይዜሽን እርሻ መልማቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በወገራ ወረዳ የኮሶዬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኖራሁን ዘገየ፤ በምርት ዘመኑ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ስንዴ ብክነትን በሚቀንስ መንገድ በመሰብሰብ 25 ኩንታል ምርት ወደ ጎተራ ማስገባታቸውን ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል የቀረበላቸው የፕላስቲክ ከረጢት በምርት አቀማመጥና አያየዝ ወቅት ነቀዝና ተባዮች የሚያደርሱትን የምርት ብክነት እንደሚከላከል ቀደም ሲል ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡


 

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ2017/18 ምርት ዘመን በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬት ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም