ከሲዳማ ክልል ከ6 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ከሲዳማ ክልል ከ6 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀረበ
ሐዋሳ ታኅሣስ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት ከ6 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ቃሬ ተናገሩ።
ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ለማሳደግም ቡናን በክላስተር የማልማት፣ ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደልና በአዲስ የመተካት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሥነ-ምኅዳርን መሠረት ያደረጉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋት ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግም ከቡና አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ከ232 በላይ ቡና አምራች ኢንዱስትሪዎች ቨርሚ ኮምፖስት አዘጋጅተው ለአርሶአደሩ እያሰራጩ ነው ብለዋል።
ዘንድሮ ከተዘጋጀው ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ቶኑ ጥቅም ላይ መዋሉን እንዲሁም ቀሪው ለመጋቢት ተከላ መቀመጡን አስረድተዋል።
በክልሉ በቡና ልማት ከተሸፈነው 176 ሺህ ሔክታር መሬት 148 ሺህ ሔክታሩ ምርት እሰጠ መሆኑም ተጠቁሟል።
በክልሉ የበንሳ ወረዳ ቡናና ፍራፍሬ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታምራት ቱንሲሳ በበኩላቸው፤ በወረዳው ካለው ከፍተኛ የቡና ልማት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል፡፡
ምርታማነቱን ለማሳደግም በወረዳው ባሉ ከ19 በላይ ቡናን የሚያዘጋጁ ኢንዱስትሪዎችና አርሶ አደሮች ማሳ ከ365 ሺህ ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት መቻሉን አንስተዋል።
ባላቸው ማሳ ውስጥ በ45 ቀን የሚደርስ ቨርሚ ኮምፖስት በማዘጋጀት ለአካባቢው አርሶ አደሮች እንደሚያሰራጩ የገለጹት ደግሞ በወረዳው ቦምቤ ቀበሌ የባሻ በቀለ ቡና ላኪ አርሶ አደር ሥራ አስኪያጅ በየነ በቀለ ናቸው።