ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር ልዩነቶቻችንን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያገኘነው የማይተካ ዕድል ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የተጀመረው ሁሉን አካታች የሆነ ሃገራዊ ምክክር ልዩነቶቻችንን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያገኘነው የማይተካ ዕድል ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ፥ ምክክር ለጋራ አሸናፊነት፣ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረመንግሥት ግንባታ! በሚል ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ለዘመናት ያለመግባባትና የንትርክ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭት ምንጭ የነበረው ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን የወለደው ችግር ነው ብሏል።

ይህን ችግር በመሠረታዊነት ለመቅረፍ እና በሀገራዊ ጉዳዮችና በብሔራዊ አጀንዳዎች ዙርያ የሚታዩ ልዩነቶችንና መካረሮችን ለማረቅ ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ ጉዳይ ነው ሲል ነው የገለጸው፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

መንግሥት አዎንታዊ የሰላም ባህል እንዲሰፍንና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ተገንብቶ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙርያ በሃሳብ አውድ ብቻ መፍታት አለባቸው የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡ለዚህም ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረው ሁሉን አካታች የሆነ ሃገራዊ ምክክር ልዩነቶቻችንን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያገኘነው የማይተካ ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል ለሁሉም አካላት የተከፈተ የትኛውንም ወገን የማይለይ አካታች የምክክር ዕድል ነው፡፡ በዚህ እድል ለመጠቀም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ዝግጁ ልንሆን ይገባል፡፡

ይህ ዕድል የኖረውን የወንድማማችነት ዕሴት ያዳከመውን የተበላሸ የፖለቲካ ባህላችንን ከማከም ባለፈ ዘላቂ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የምክክር ዕድሉ በመሰረታዊ ጉዳዮቻችን ዙርያ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ፣እየዳበረ የሚሄድ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ብሎም በመሃከላችን የእርስ በእርስ መተማመንን በመፍጠር የህዝቦችን መተባበር እና አንድነት በማረጋገጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ጦርነትና አብዮት የተሟላ መፍትሔ የማያመጡ መሆናቸውን በተግባር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ የመጣ አሸናፊነት ጊዜያዊና መልሶ ቁርሾና ቂምን የሚያሳድር መንገድ መሆኑን ተምረንበታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በውይይትና በምክክር ችግሮቻቸውን አለመግባባቶቻቸውን የመፍታት ድንቅ ባህል የነበራቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ እሴት እየጎለበተ በመጣው ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ምክንያት ከጊዜ ወደጊዜ በመደብዘዝ ከፋፋይ ነጠላ ትርክት መገለጫችን እስከመሆን ደርሷል፡፡

በአለም ላይ በርካታ ሀገራት ከከረረ ልዩነትና ከግጭት ድባብ ለመውጣት ሀገራዊ ምክክር እንደመፍትሄ ተጠቅመዋል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ይህንን ማድረግ የማይሳነን ሕዝቦች ለመሆናችን በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ ዕሴቶቻችን ማሳያ ናቸው፡፡

ስለሆነም ዘላቂ የሆነ መፍትሔን ለማምጣት በእውነተኛ ፖለቲካዊ መሻት በቅንነት ለውይይት ለሰጥቶ መቀበልና ለጋራ መፍትሔ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መነሳት ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያውያን የመጣንበት የግጭትና የጦርነት አዙሪት በቃን የምንልበት ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፡፡ ግጭት ማንንም አሸናፊ የማያደርግ የጥፋት አዙሪት ስለሆነ የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ስኬታማ ማድረግ ፣ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትሆን ሀገር ለመገንባትና ሁላችንንም የጋራ አሸናፊ ለማድረግ ያግዘናል፡፡

በመሆኑም ሁሉም አካል በምክክሩ በንቃት እንዲሳተፍ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

ምክክር ለጋራ አሸናፊነት፣ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረመንግሥት ግንባታ!

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም