ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ዋንጫ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ዋንጫ
ክፍል ሁለት የቀጠለ
የኢትዮጵያ ዘጠነኛ ተሳትፎ በአህጉራዊው መድረክ
እ.አ.አ 1982 ኢትዮጵያ በሊቢያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለዘጠነኛ ጊዜ ተሳትፎዋን ማድረግ ቻለች።
በውድድሩ ላይ አሁንም ስምንት አገራት ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከአልጄሪያ፣ዛምቢያና ናይጄሪያ ጋር ተደልድላ ጨዋታዎቿን አድርጋለች።
በምድብ ጨዋታዎቹ በናይጄሪያ 3 ለ 0 እንዲሁም በዛምቢያ 1 ለ 0 የተሸነፈች ሲሆን ከአልጄሪያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።
ኢትዮጵያ በምድቧ አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።
በፍጻሜው ጨዋታ ጋና ሊቢያን በመለያ ምት በማሸነፍ ለሶስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አንስታለች።
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካው ዋንጫ የተመለሰችበት ታሪካዊ ሁነት
ኢትዮጵያ ከ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ በአህጉራዊው የእግር ኳስ ውድድር መድረክ ለመሳተፍ ሶስት አስርት ዓመታታን መጠበቅ ግድ ሆኖባታል። በነዚህ 30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 15 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ተካሄደዋል።
እ.አ.አ በ2013 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ ውድድሩ ዳግም ተመለሰች።
ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈችበት መንገድ ልብ አንጠልጣይ ነበር።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2012 በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከሱዳን ጋር ባደረገችው የመጨረሻ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ በመጀመሪያ ዙር ኦምዱርማን ላይ 5 ለ 3 በሆነ ውጤት ተሸንፋለች።
ሱዳን ጨዋታውን ያሸነፈችው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ሁለት አጨቃጫቂ የፍጹም ቅጣት ምት በግቦች ነበር።
ጥቅምት 4 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ በስታዲየሙ ዙሪያ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ በርካታ ተመልካች ተሰልፎ ነበር።
ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም መጠናቀቁ በስታዲየሙ የተገኘውን ተመልካች ጭንቅ ውስጥ ከቶ ነበር። ጭንቀቱ በስታዲየሙ ላሉት ብቻ ሳይሆን በቴሌቪዥን መስኮት ለሚከታተሉት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት ዋልያዎቹ አዳነ ግርማ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ቻሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫው ለመሳተፍ አንድ ተጨማሪ ጎል ያስፈልጋታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ወሳኟን ሁለተኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳረፈ። ግቡ ሲቆጠር በስታዲየሙ ተመልካቾች ላይ የነበረው ስሜት በከፍተኛ ደስታ የተሟላ ሲሆን ስሜታቸውንብ በእንባ የገለጹም ነበሩ።
ጨዋታው በድምር ውጤት 5 ለ 5 ተጠናቆ ከሜዳ ውጪ ብዙ ባስቆጠረ በሚል ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስ ቻለች።
ከጨዋታው በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም፣በመስቀል አደባባይና በመዲናዋ የተለያዩ አውራ ጎዳናዎች፣መንደሮችና የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ክፍሎች የነበረው የደስታ ስሜትና ፈንጠዝያ የሚረሳ አልነበረም።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የደስታው ተቋዳሽ ነበሩ።
ኢትዮጵያን ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንድትመለስ ያደረጉት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ነበሩ።
ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 16 አገራት በስድስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ኢትዮጵያም በምድብ ሶስት ከቡርኪናፋሶ፣ናይጄሪያና ዛምቢያ ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን አድርጋለች።
በመጀመሪያ ጨዋታዋ ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር አንድ አቻ ተለያይታለች። አዳነ ግርማ በ65ኛው ደቂቃ ለኢትዮጵያ ግቡን አስቆጥሯል።
በሁለተኛው ጨዋታ ኢትዮጵያ በቡርኪናፋሶ የ4 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዳለች።
በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ በናይጄሪያ 2 ለ 0 ተሸንፋለች።
ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛ ከምድቧ ሳታልፍ ቀርታለች።
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ብትመለስም በውድድሩ ላይ ያስመዘገበችው ውጤትና ያሳየችው ብቃት የእግር ኳስ ቤተሰቡን ያስደሰተ አልነበረም።
ይሁንና ብሔራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ ሲመለስ በአዲስ አበባ ስታዲየም በበርካታ ደጋፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል።
በፍጻሜው ጨዋታ ናይጄሪያ ቡርኪናፋሶ 1 ለ 0 በማሸነፍ የአፍሪካን ዋንጫን ለሶስተኛ ጊዜ አንስታለች።
ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈችበት የአፍሪካ ዋንጫ
ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ2021 ካሜሮን ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።
ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሰችው ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጅ አገር ካሜሮን፣ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን አድርጋለች።
ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በኬፕቨርዴ 1 ለ 0 ተሸንፋለች።
በሁለተኛው ጨዋታ ዋልያዎቹ በአዘጋጇ አገር ካሜሮን 4 ለ 1 ተሸንፈዋል።
በጨዋታው ኢትዮጵያ አጥቂው ዳዋ ሁቴሳ በአራተኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ብትችልም ቪንሰንት አቡበከርና ቶኮ ኢካምቢ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የማይበገሩትን አንበሶች አሸናፊ አድርገዋል።
በወቅቱ በአሰልጣኝ ውበቱ የተመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ከቡርኪናፋሶ ጋር አንድ አቻ ተለያይታለች። ለብሔራዊ ቡድኑ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ በፍፁም ቅጣት ምት ነበር።
ኢትዮጵያ በምድቡ አንድ ነጥብ ብቻ በማግኘት ከምድቧ የመጨረሻውን ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በቁጥሮች
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የ11 ጊዜ ተሳትፎ ኢትዮጵያ 31 ጨዋታዎችን አድርጋ 8ቱን ስታሸንፍ 19 ጊዜ ተሸንፋለች። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥታለች።
በነዚህ 31 ጨዋታዎች ኢትዮጵያ 33 ግቦችን ስታስቆጥር 67 ጎሎችን አስተናግዳለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ በሰፊ ግብ ያሸንችባቸው ጨዋታዎች ሁለት ናቸው። እ.አ.አ በ1962 ራሷ አዘጋጅታ ራሷ በወሰደችው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቱኒዚያና ግብጽን በተመሳሳይ 4 ለ 2 አሸንፋለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫው በሰፊ የግብ ልዩነት የተሸነፈችው እ.አ.አ በ1970 ሱዳን ባዘጋጀችው ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን በወቅቱ በኮትዲቭዋር 6 ለ 1 በሆነ ውጤት ተረታለች።
ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ በውድድሩ ተሳትፎዋ ከፍተኛ ግብ ያስተናገደችበት ሲሆን 12 ጎሎች ተቆጥረውባታል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ከፍተኛ ግቦችን ያስቆጠረችባቸው ውድድሮች እ.አ.አ በ1952 እና በ1968 በቅደም ተከተል ሶስተኛውንና ስድስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ባዘጋጅበት ወቅት ነው። በነዚህ ውድድሮች ላይ በተመሳሳይ ስምንት ግቦችን አስቆጥራለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ሶስት ጊዜ አዘጋጅታለች።
ኢትዮጵያውያኖቹ አጥቂዎች ሉቺያኖ ቫሳሎና መንግስቱ ወርቁ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተመሳሳይ 8 ግቦችን በማስቆጠር በአፍሪካ ዋንጫ የምንጊዜም የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ዝርዝር ውስጥ 21ኛ እና 22ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ ሞሮኮ እየተካሄደ በሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አትሳተፍም።
የአፍሪካ እግር ኳስ መስራችና ፈር ቀዳጅ እየተባለች የምትጠራው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዎቿ ከሰሜን፣ደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ብርቱ ፉክክር በማድረግ መልካም የሚባል ውጤት አስመዝግባለች።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአፍሪካ ዋንጫ ያላት ተሳትፎ እየተቀዛቀዘ መጥቶ ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ማለፍ እየተሳነው ነው።
የስፖርት ቤተሰቡና ተንታኞች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት አለመቻሉ፣የእግር ኳስ እድገቱ ወደ ኋላ መቅረቱ፣ የአጥቂ መስመሩ ክፍል የአጨራረስ ድክመት፣ ለወጣት ተጫዋቾች እድል አለመስጠት፣የአሰልጣኞች በየጊዜው መለዋወጥ፣ለእገር ኳሱ የሚሰጠው ትኩረት የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑና እግር ኳሱ በስፖርቱ ባለፉ ሰዎች አለመመራቱን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ይቀመጣሉ።
ጠንካራና ተወዳዳሪ ቡድን የመገንባት ስራ ትኩረት ያሻዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2029 የሚካሄደውን 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥያቄ ማቅረቧ የሚታወቅ ነው።
በዚህም ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፍ ጠንካራና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን መገንባት የሚያስችል "ሮድ 2029" የታዳጊዎች እግር ኳስ የስልጠና ፕሮጀክት ተጀምሯል፡፡
“ሮድ 2029"ን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ከሁሉም አካባቢዎች 85 ብቃት ያላቸው ታዳጊዎች ተመርጠው ለዘጠኝ ወራት ስልጠና ወስደው ብቃት ያላቸው ተመርጠዋል፡፡
ከእነዚህ ታዳጊዎች መካከል 26ቱ በብቃታቸው ተመርጠው የ"ሮድ 2029" ግብን ማሳካት የሚያስችል የክፍል ውስጥ እና የሜዳ ላይ ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ታዳጊዎቹ ኢትዮጵያ በህዳር ወር ባስተናገደችው ከ17 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበር ምክር ቤት ዞን (ሴካፋ) ተሳትፎ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ላይ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በሞሮኮ በሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ይታወቃል።
"ሮድ 2029" የታዳጊዎች እግር ኳስ የስልጠና ፕሮጀክት በአሜሪካዊ እና ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች ጥምረት የሚካሄድ ሲሆን በኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
በዲጂታል አማራጮች ተደግፎ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የሚሰጥ ሥልጠና መሆኑን በማንሳት፤ በእስካሁኑ ሂደት ተስፋ ሰጭ ውጤት ታይቶበታል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት እንድትመረጥ የቴክኒክ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
ታዳጊዎችን እግር ኳስ ልማት፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን እንዲያሞሉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋት ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች ነው።
መንግስት የጀመራቸው ስራዎች በተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይኖርባቸዋል። አጠቃላይ የእግር ኳሱ እደግት የስፖርት ባለድርሻ አካላትን የጋራ ትብብር ይጠይቃል።
ተስፋ ሰጪ እና ብርሃን ፈንጣቂ ጅማሮዎችን ነገ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም መድረክ በእግር ኳሱ ስኬታማ ለመሆን መሰረት የሚጥሉ ናቸው።