ባህላዊ እሴቶችን በጥናት በማስደገፍ ለጋራ ትርክት ግንባታ ለማዋል በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ እሴቶችን በጥናት በማስደገፍ ለጋራ ትርክት ግንባታ ለማዋል በቅንጅት እየተሰራ ነው
አምቦ ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ ባህላዊ እሴቶችን በጥናት በማስደገፍ ለጋራ ትርክት ግንባታ ለማዋል በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በሀገር በቀልና ኪነጥበብ ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት በወቅቱ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የኦሮሞ ህዝብ ታሪክና ባህል እሴቶችን በጥናት በማስደገፍ ለጋራ ትርክት ግንባታ ለማዋል እየሰራ ነው፡፡
የመደጋገፍ የባህል እሴቶችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ለትውልድ ለማስተላለፍና ይበልጥ ለማስተዋወቅ ከሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የባህል እሴቶቹ ለትውልድ እንዲተላለፉና በትምህርት ስርአት ውስጥ እንዲካተቱ እንዲሁም በመጽሃፍት እንዲታተሙ ምክረሀሳብ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
በጥናትና ምርምር ተደግፈው የተጻፉ የህትመት ውጤቶችም ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ሳሙኤል ሌይኩን (ዶ/ር) ፤ ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው በሀገር በቀል የኪነጥበብ ኮንፍረንስ ላይ የኦሮሞን ህዝብ የመተጋገዝ ባህል በኪነጥበብ ስራዎች ላይ የተቃኙበትን አውድ የሚያስረዳ ጥናት ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል።
የምርምር ውጤቶች ትውልዱ ባህላዊ እሴቱን በመረዳት ባህሉንና ቋንቋውን እንዲያዳብር ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ባይሳ ለታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል የባህል እሴቶችን በማጥናት ለህብረተሰብ ግንባታ የሚውሉበትን ሂደት ለማሳለጥ ከኪነ ጥበብ ስራዎች ጋር ለማስተሳሰር መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
ባህልን ከኪነ ጥበብ ስራዎች ጋር ማቀናጀት በሀገራዊ እድገት ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወት በመሆኑ የኮንፍረንሱ መካሄድ ይህን ለማሳካት ልምድ የሚወሰድበት ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተሰማ ታአ፤ የባህልና የታሪክ እሴቶችን በማጥናት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማዋል መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ባህላዊ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍም መሰል የባህል የምርምር ኮንፍረንሶች ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተመራማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡