ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት የወጣቶችን የላቀ አቅም የምትፈልግበት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት የወጣቶችን የላቀ አቅም የምትፈልግበት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን "ባሕር በራችን የደም ሥራችን" በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የወጣቶች የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ እንደገለጹት፤ ወጣቶች ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።


 

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቷን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት የወጣቶችን የላቀ አቅም የምትፈልግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ የሆነው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለማሳካት ደማቅ ታሪክ የሚጻፍበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች ይህንን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ጥያቄ በሚገባ ተረድተው በዕውቀትና በሰለጠነ መንገድ ድምፃቸውን ሊያሰሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር የማይነጣጠሉ ናቸው ብለዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላትን የጠበቀና የማይነጠል ትስስር ምላሽ ለማስገኘት ወጣቶች ታሪካዊና ተፈጥሯዊ እውነትን በሚገባ ተገንዝበው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት የምታደርገው ጥረት የታሪክ፣ የሕግ እና የተፈጥሮ መብትን መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


 

ወጣቶች በዕውቀትና ዲፕሎማሲያዊ መንገድን በመረዳት የሀገርን ብሄራዊ ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሣታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ታረቀኝ አብዱልጀባር፤ ወጣቶች ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ሁኔታ በመረዳት የኢትዮጵያን ዕውነት በዓለም መድረኮች የማስተጋባት ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጿል።


 

የባሕር በር ጥያቄን ጨምሮ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በጋራ ለማሳካት የበኩላቸውን አዎንታዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።


 

በቀጣይም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እውን ለማድረግ አስፈላጊውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም