ቀጥታ፡

የህክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷል

ሰመራ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦የበሽታ መከላከል ፖሊሲን ከመተግባር በተጓዳኝ  የህክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ፡፡

የጤና ሚኒስቴር በአፋር ክልል የጤና አገልግሎትን ተደራሸ ለማድረግና የእናቶች ወሊድ አገልግሎትን ለማሳለጥ የሚያግዙ ሦስት አምቡላንሶችን  በድጋፍ  አበርክቷል።

የጤና ሚኒስቴር አምቡላንሶቹን በክልሉ ለዱብቲ፣ አይሳኢታና መሐመድ አክሌ መታሰቢያ ሆስፒታሎች  አስረክቧል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ድጋፉን ባስረከቡት ወቅት እንዳሉት፤ሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከል ፖሊሲን ከመተግባር በተጓዳኝ   የህክምና  አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳካት ትኩረት ሰጥቷል።

የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥም ለሰው ሀይል ልማትና የህክምና ተቋማትን ግብአት ለማሟላት በቅንጅት መሰራቱን አክለዋል።

የጤና አገልግሎት ተደራሸነትና ጥራትን በማሳካት የእናቶችና ህፃናት ጤናን ለመጠበቅ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ በአፋር ክልል የጤና  አገልግሎትን ተደራሸ ለማድረግና የእናቶች ወሊድ  አገልግሎትን ለማሳለጥ የሚያግዙ አምቡላንሶችን ዛሬ ድጋፍ ማድረጉም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በአፋር ክልል  የጤና ስርዓቱን በማሻሻል ቀልጣፋ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ድጋፉ እንደሚጠናከር አመላክተዋል።  

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ፤ ለሆስፒታሎቹ የተደረገው የአምቡላንስ ድጋፍ  ለህብረተሰቡ ፈጣንና አስተማማኝ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአምቡላንሶቹ ድጋፍ በተለይ የእናቶችን የወሊድ የህክምና አገልግሎትን ለማሳካት የማይተካ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።


 

የአምቡላንስ ድጋፉን ከተረከቡ የሆስፒታል ሀላፊዎች መካከል  የዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሁሴን ኡመር በበኩላቸው፤ የተደረገው ድጋፍ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ጥራቱን የሚያሳድግ መሆኑን ገልፀዋል።

በአምቡላንሶች ርክክብ ስነ ስርአት ላይ  የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባን ጨምሮ የክልሉ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም