የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማከናወኑን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማከናወኑን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡
ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል አስመልክቶ የተቋሙን አጠቃላይ ሀገራዊ አበርክቶ የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡበት ሲምፖዚየም ተካሂዷል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 75 ዓመታት በሀገሪቷ የሰው ኃይል ልማት፣ በጤና፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ለሀገር ያበረከተውን አስተዋጽኦ የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ጄይሉ ዑመር (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ዩኒቨርሲቲው ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ምሁራን ያፈራ አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል።
ተቋሙ በቀጣይም ጥራት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራትና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዓለሙ መኮንን በሲምፖዚየሙ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አሥርተ ዓመታት በሀገሪቷ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመድ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ጠንካራ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የታሪክ ምሁሩ ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ ያለበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።