ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ 32 ሚሊዮን ማሳዎች በዲጂታል የመረጃ  ሥርዓት ተደራጅተዋል

አርባ ምንጭ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ 32 ሚሊዮን ማሳዎች በዲጂታል የመረጃ ሥርዓት መደራጀታቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር ሥርአትን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ትዕግስቱ ገብረመስቀል እንዳሉት፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዙ የግብርና መረጃዎችን እንደ የአፈር መረጃ፣ የአየር ፀባይ ሁኔታ፣ የማዳበሪያ አቅርቦት እና የመሬት መጠቀሚያ ስርአት አገልግሎትን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ይህም ግብርናውን ለማዘመንና የአርሶና አርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እንደሚያግዝ  ገልጸዋል።

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያም የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ የአርሶና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

አርሶና አርብቶ አደሮች የመሬት ይዞታቸውን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በተደረገው ጥረት በእስካሁኑ ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ  32 ሚሊዮን ማሳዎች በዲጂታል ስርአት እንዲደራጁ መደረጉንም አቶ ትዕግስቱ ገልጸዋል።

በተለይም አርሶና አርብቶ አደሮች የመሬት ይዞታቸውን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዲችሉና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ከፋይናንስ አገልግሎት ጋር ማስተሳስር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ዲጂታል የፋይዳ መታወቂያ ያግዛቸዋል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ፤ በክልሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን የመሬት አስተዳደር ወደ ዲጂታል ስርአት በማስገባት ተጠቃሚነቱን ለማላቅ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።


 

የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች የዲጂታል መሬት አስተዳደር ስርአቱ ተጠቃሚ ለመሆንም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

የመሬት አስተዳደር ስርአትን ለማዘመን በተደረገ ጥረት በ869 ሺህ 211 አባወራና እማወራዎች እጅ ያለ ከ2 ሚሊዮን በላይ መሬቶች በዲጂታል ስርአት እንዲደራጅ መደረጉንም ገልጸዋል።

ይህን አጠናክሮ ለመቀጠልም በሚቀጥሉት አንድ መቶ ቀናት በክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አርሶና አርብቶ አደሮች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።


 

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እያገዘ ነው ያሉት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ አስተባባሪ ደጀኔ ገብሬ ናቸው።

ዲጂታል መታወቂያ ለአርሶና አርብቶ አደሮች  የብድር አገልግሎቶችን በማግኘት በስራቸው ውጤታማ  እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ ላይ የፌደራል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የዞኖችና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም